በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል በታንዛኒያ ይደረጋል የተባለው የሰላም ድርድር፣ ትላንት ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚጀመር፣ ሁለቱም አካላት ያረጋገጡ ቢኾንም፣ ድርድሩ በርግጥም ስለመጀመር አለመጀመሩ እስከ አሁን በይፋ የታወቀ ነገር የለም፡፡
በአፍሪካ ኅብረት ኮሚሽን የፖለቲካ፣ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዴኦዬ፣ ኅብረቱ በአፍሪካ ሰላም እና ጸጥታ ጉዳዮች ላይ የሚያከናውናቸውን ተግባራት በተመለከተ፣ ዛሬ በበይነ መረብ ለጋዜጠኞች መግለጫ በሰጡበት ወቅት፣ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት መካከል፣ በታንዛኒያ ይደረጋል የተባለው ድርድር ተጀምሮ እንደኾነና ሒደቱ በምን ደረጃ ላይ እንደሚገኝ፣ ከአሜሪካ ድምፅ ጥያቄ ቢቀርብላቸውም፣ ቀጥተኛ ምላሽ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡
ኾኖም ኮሚሽነሩ፣ ለጥያቄው በሰጡት አስተያየት፣ ችግሩን በሰላም ድርድር ለመፍታት የተጀመረው ጥረት የሚደነቅ እንደኾነ ገልጸዋል፡፡ “ግባችን እ.አ.አ. በ2030 የመሣሪያ ድምፆችን ኹሉ ዝም ማሰኘትና ኹሉም ግጭቶች እንዲቆሙ ማድረግ ነው፤” ያሉት ኮሚሽነሩ፣ “ስለዚኽ በኢትዮጵያም ይኹን በሌላ ማንኛውም የኅብረቱ አባል ሀገር፣ ለሕዝቦቻችን ጥቅም ሲባል፣ እንዲሁም ዐቅማችንን ሁሉ የምንፈልጋትን አፍሪካ እውን በማድረግ ተግባር ላይ ማዋል ይቻል ዘንድ፣ ግጭቶችን ለመፍታት የሚወሰዱ ርምጃዎች የሚደነቁ ናቸው፤” ብለዋል፡፡
ከኢትዮጵያ አልፎ ለመላው አፍሪካ ተምሳሌት እንደኾነ የጠቀሱት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት፣ በሀገሪቱ ለሚንቀሳቀሱ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች መነሣሣትን እንደሚፈጥር ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡ “የፕሪቶሪያው ስምምነት ተኣምራዊ ስምምነት እየተባለ ነው፡፡ ምክንያቱም፣ ላለፉት ስድስት ወራት ምንም ዐይነት ጥይት አልተተኮሰም፡፡ በመኾኑም ስምምነቱ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ላሉ ሌሎች ታጣቂ ቡድኖች ትልቅ መነሣሣት ይኾናል ብዬ አምናለኹ፤” ሲሉም ተናግረዋል።
የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ቃል አቀባይ ኑር መሐሙድ ሼኽ ደግሞ፣ በጽሑፍ በሰጡን አጭር ምላሽ፣ “እኛ የምናውቀው ንግግሩን የመጀመሩ ሒደት የላቀ ደረጃ ላይ እንደሚገኝና ንግግሮቹ በታንዛኒያ እንደሚደረጉ ነው፤” ብለዋል፡፡ “ሒደቱ በኢትዮጵያውያን ባለቤትነት የሚመራ ነው፤” ሲሉ በጽሑፋቸው ገልጸዋል።
የኢጋድ ሥራ አስፈጻሚ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ፣ ስለ ኹኔታው “ጥሩ ግንዛቤ” እንዳላቸውና “በፓርቲዎቹ ከተፈለጉ ድጋፍ ለማድረግ” እንደተዘጋጁ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት እና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት፣ በታንዛኒያ እንደሚነጋገሩ ከመታወቁ ባለፈ፣ ተደራዳሪ ወገኖች በማን እንደሚወከሉ፣ ስለ አደራዳሪዎች ማንነት፣ እንዲሁም ስለ ድርድሩ ሒደት፣ መንግሥት እና ታጣቂው ቡድኑም ኾኑ የታንዛንያ ባለሥልጣናት፣ ዝርዝር ጉዳዮችን ከመግለጽ መቆጠባቸውን ሮይተርስ አመልክቷል።
የአሜሪካ ድምፅ፣ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል፣ አስተያየት ለማግኘት በተደጋጋሚ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም፡፡
በአሶሺየትድ ፕሬስ የተጠቀሱት የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ቃል አቀባይ ኦዳ ተርቢ ግን፣ “ለዋናው ድርድር መንገድ የሚጠርግ” ያሉት “የመጀመሪያ ውይይት መጀመሩን” ጠቅሰዋል፡፡ "የአሁኑ ንግግር ትኩረት፥ መተማመንን መፍጠር እና አቋሞችን ግልጽ ማድረግ ነው፤" ማለታቸውን፣ እንዲሁም ኖርዌይ እና ኬንያ፣ በዚኽ ሳምንት የሚደረገውን ንግግርም እንደሚያሸማግሉ መግለጻቸውን አሶሺየትድ ፕሬስ በዘገባው ጠቅሷል፡፡
በታንዛኒያዋ የዛንዚባር ደሴት በሚካሔደው ድርድር የኢትዮጵያን መንግሥት በመወከል ከሚሳተፉት መካከል፣ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደኅንነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሑሴንና የፍትሕ ሚኒስትሩ ዶ/ር ጌዴዎን ጢሞቴዎስ እንደሚገኙበት፣ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ሁለት ምንጮች ለሮይተርስ ተናግረዋል፡፡ የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ተወካዮችን ማንነት በተመለከተ ግን፣ እስከ አሁን በዘገባዎች አልተጠቀሰም፡፡
/ሙሉ ዘገባውን በድምፅ ለማድመጥ የተያያዘውን ፋይል ይጫኑ/