በታንዛኒያ የንግድ ከተማ ዳሬ ሰላም ሊካሄድ የታሰበውን ተቃውሞ ለማስቆም፣ የተቃዋሚ ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ሰኞ እለት መታሰራቸውን ቻዴማ የተሰኘው ተቃዋሚ ፓርቲ አስታውቋል።
ሰልፉ ቢታገድም፣ የቻዴማ ፓርቲ አባሎቹ በጸጥታ አካላት መታገታቸውን እና መገደላቸውን አስመልክቶ ያዘጋጀውን ሰልፍ እንደሚያካሂድ አስታውቋል።
ቻዴማ፣ ዋና ሊቀመንበሩ ፍሪማን ምቦዌ እና ምክትላቸው ቱንዱ ሊሱ ሰኞ እለት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ገልጾ የታቀደው ሰልፍ እንዳይካሄድ በከተማዋ ቁልፍ ቦታዎች አድማኝ በታኝ ፖሊሶች መመደባቸውንም አመልክቷል።
ምቦዌ በፖሊስ ተይዘው ከመወሰዳቸው በፊት "ሰልፍ ማካሄድ ህገመንግስታዊ መብታችን ሆኖ ሳለ ህዝብን ለማስፈራራት እና ነፃነታችንን ለማፈን ፖሊስ እየተጠቀመ ያለው የኃይል መጠን አስገርሞናል" ሲሉ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል።
ቻዴማ ፕሬዝዳንት የሳሚያ ሱሉሁ ሀሰን መንግስት ሀገሪቱን ወደ ቀድሞው ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ አፋኝ ስርቶች እየመለሷት ነው ሲል ይከሳል።
መድረክ / ፎረም