ዋሺንግተን ዲሲ —
ዩናይትድ ስቴትስና ታሊባን፣ ሩሰያ ነገ አርብ ሞስኩ ውስጥ በምታስተናግደው የጋራ ጉባዔ ላይ እንደሚሳተፉ ተገለጸ። ጉባዔው ለአፍጋኒስታን ዘላቂ ሰላም የሚበጀውን ለመምከር እንደሆነም ታውቋል።
የሩስያ ውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማሪያ ዛኻሮቭ ዛሬ በጉባዔው ዋዜማ በሰጡት ቃል፣ ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ የተለያዩ 11 ሀገሮች ልዑካን፣ በሞስኮው የምክክር መድረክ ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ቃል አቀባይዋ እንደገለጹት፣ ጉባዔው ለጋራ ውይይትና ምክክር ምቹ ሁናቴን በመፍጠር ላይ የሚያተኩር ይሆንና፣ ለአፍጋኒስታን ችግሮችም በተቻለ ፍጥነት ስምምነት ላይ የተደረሰበት መፍትሔ የሚያቀርብ ይሆናል።
ባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ጉባዔ እዚያው ሞስኮ ላይ ታቅዶ የነበረ ሲሆን፣ ዋሺንግተንም ሆነች ታሊባን ግብዣውን እንዳልተቀበሉ አይዘነጋም።
የፌስቡክ አስተያየት መስጫ