ቪኦኤ ዜና —
እስላማዊው ቡድን አፍጋኒስታንን በተቆጣጠረበት የመጀመሪያ ዓመት ዋዜማ የትምህርት፣ የስራ እና የፖለቲካ ተሳትፎ መብቶችን ለመጠየቅ እና አገዛ ዙን ለመቃወም ዛሬ ቅዳሜ አደባባይ የወጡ ሰዎችን ለመበተን ካቡል የሚገኙ የመንግስቱ የጸጥታ ኃይሎች ወደ ሰማይ መተኮሳቸው እና በሴቶች ላይም ድብደባ መፈጸማቸው ተዘገበ።
ብዙም የማይፈር በሚመስለው በዚህ የታሊባን ኃይሎችን ለመቃወም የተካሄደ ትዕይንት፡ በአፍጋኒስታን ዋና ከተማ ወደ ሚገኘው የትምህርት ሚኒስቴር ያመራው ሰልፍ የመንግስቱ ኃይሎች የኃይል እርምጃ ከመስጠታቸው አስቀድሞ በነበረው ጊዜ ሰልፈኞቹ “ስራ፣ ዳቦ እና ነፃነት እንፈልጋለን” የሚሉ መፈክሮችን ሲያሰሙ ተስተውለዋል።