የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዥ ዓለም አቀፍ ተቆጣጠሪዎች የዛፖሪዚያን የኒዩክለር ማብለያ ተቋም እንዲፈትሹ ፈቃድ እንዲሰጣቸው ጠየቁ፡፡
የዋና ጸኃፊው ጥያቄ የመጣው ሩሲያና ዩክሬን በቅርቡ በፋብሪካው ላይ ለተነሰዘረው የከባድ መሳሪያ ጥቃት እርስ በርስ መወነጃጀል ከጀመሩ ወዲህ መሆኑ ተመልክቷል፡፡
ጉተሬዥ “በኒዩከለር ተቋሙ ላይ የሚካሄድ ማናቸውም ጥቃት “ራስን ማጥፋት ነው” ሲሉ በጃፓን ለሪፖርተሮች በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ተናግረዋል፡፡
ሞስኮ “የኒዩከለር ሽብር እያካሄደች ነው” የምትለዋ ዩክሬን፣ በአውሮፓ ትልቁ በሆነው የኒዩክለር ኃይል ተቋም ላይ የቦምብ ጥቃት አድርሳለች ስትል ትናንት እሁድም ሩሲያን በድጋሚ ከሳለች፡፡
ሩሲያ የምታካሄደው የኒዩከለር ሽብር የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ጠንካራ ምላሽ ይፈልጋል ሲሉ ትዊት ያደረጉት የዩክክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎድሚር ዜለንስኪ “በሩሲያ የኒዩክለር ኢንደስትሪ እና የኒዩክለር ነዳጅ ላይ ማእቀብ መጣል ያስፈልጋል” ብለዋል፡፡
በሩሲያ ቁጥጥር ስር ባለ የዩክሬን ግዛት ውስጥ የሚገኘው የኒዩክለር ተቋም፣ ባላፈው ዓርብ ጥቃት የደረሰበት መሆኑን ተነገሯል፡፡
ሞስኮ ጥቃቱን ያደረሰችው ዩክሬን ናት ስትል ከሳለች፡፡