በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ማንም ከሕግ በላይ መኾን አይችልም" የሶሪያ የኃይማኖት ተኮር ጥቃቶች መርማሪ ኮሚቴ


የሶሪያ መርማሪ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ያሲር አል ፋርሃን መግለጫ ሲሰጡ፣ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም.
የሶሪያ መርማሪ ኮሚቴ ቃል አቀባይ ያሲር አል ፋርሃን መግለጫ ሲሰጡ፣ መጋቢት 2 ቀን 2017 ዓ.ም.

በሶሪያ የጦር ሠራዊት እና በቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ባሻር አል አሳድ ታማኞች መካከል የሚካሄደውን ውጊያ የሚመረምረው ኮሚቴ "ማንም ከሕግ በላይ አይኾንም፥ የድርጊቱን ተጠያቂዎች በሙሉ ታስረው ሕግ ፊት እንዲቀርቡ እናደርጋለን" ሲል ተናገረ።

ብዙኅኑ ነዋሪዎች ከሥልጣን የተወገዱት ፕሬዝደንት ኃይማኖታዊ ማኅበረሰብ "አላዊቶች" በሆኑባቸው መንደሮች ብዙ መቶ ሲቪሎች መገደላቸውን ዕማኞች እና የጦርነት ተከታታይ ቡድን ሪፖርቶች ያመለከቱ ሲሆን በአክራሪ እስልምና አቀንቃኞች የሚመራው የሶሪያ መንግሥት ምርመራ እንዲከፍት ግፊቱ በርትቶ ቀጥሏል።

የመርማሪ ኮሚቴው ቃል አቀባይ ያሲር ፋርሃን ዛሬ ማክሰኞ በቴሊቭዥን በተላለፈ ጋዜጣዊ ጉባኤ ላይ ሲናገሩ" ማንም ከሕግ በላይ መሆን አይችልም። የምርመራችንን ውጤት ለፕሬዝደንቱ እና ለፍትሕ ተቋሙ እናቀርባለን" ብለዋል። መርማሪ ኮሚቴው ዕማኞችን እና የጥቃቱን ተጠርጣሪዎች ቃል ተቀብሎ በቂ ማስረጃ ያገኘባቸውን ተጠርጣሪዎች ለፍትሕ አካሉ እንደሚያስተላልፍ አስታውቀዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን እንዳመለከተው የመንግሥቱ ጦር በጠረፉ ግዛት በአሳድ ታማኞች ላይ በከፈተው ኃይማኖት ተኮር ዘመቻ ቤተሰቦች ሴቶች እና ሕጻናትን ሳይቀሩ ተገድለዋል።

የሶሪያ የሽግግር ፕሬዝደንት አሕመድ አል ሻራ ትላንት ሰኞ በሰጡት ቃለ መጠይቅ የቀድሞዎቹን ሽምቅ ተዋጊ ቡድኖች በአንድ ተቋም ሥር ያዋሃደው የሀገሪቱ የመከላከያ ሚንስቴር ሠራዊት በግድያው ተሳትፎ እንደሁ ለመናገር አልችልም ማለታቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል።

ብጥብጡ የተቀጣጠለው በጠረፉ ክፍለ ግዛት ያሉት የመንግሥቱ ኃይሎች በአሳድ መንግሥት ርዝራዦች ጥቃት እንደተከፈተባቸው የመንግሥቱ ባለሥልጣናት ሐሙስ ዕለት መናገራቸውን ተከትሎ ነው።

በሱኒ እስልምና አክራሪዎች የሚመራው መንግሥት " የአሳድ መንግሥት ቅሪቶች በሚገባ የተዘጋጁበት ገዳይ ጥቃት" ያለውን ለመደምሰስ ብዛት ያለው ጦር ወደአካባቢው አዝምቷል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG