በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

"ዩናይትድ ስቴትስ እና ቱርክ በሦሪያ ጉዳይ የሚስማሙባቸው በርካታ ጉዳዮች አሉ" - ብሊንከን


የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን አንካራ፣ ቱርክ እአአ ታኅሣሥ 13/2024
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን፣ የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን አንካራ፣ ቱርክ እአአ ታኅሣሥ 13/2024

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ አርብ ከቱርኩ አቻቸው ጋራ አንካራ ላይ ተገናኝተው ከተነጋገሩ በኋላ በሰጡት አስተያየት ነው፤ በዐዲሱ የሦሪያ መንግሥት እውን ኾነው ማየት በሚፈልጓቸው ጉዳዮች ዙሪያ የሚስማሙባቸው በርካታ ጉዳዮች መኖራቸውን ተናግረዋል።

ብሊንከን እና የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሃካን ፊዳን በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ ሁለቱ ሀገራት በሦሪያ “ሁሉን አቀፍ እና ከወገንተኝነት የጸዳ፤ የህዳጣን ማኅበረሰቦችን እና የሴቶችን መብት የሚያስከብር፣ ለሕዝብ ተቋማት ጥበቃ መረጋገጥ የሚቆምና እና ሕዝብ የሚያስፈልገውን እንዲያገኝ ለማድረግ የሚሠራ ጊዜያዊ መንግሥት እንዲቋቋም ይፈልጋሉ” ብለዋል።

ብሊንከን አክለው እንደገለጹት፤ ሁለቱ ሀገራት ጊዜያዊው የሦሪያ መንግሥት ከቀድሞው የሦሪያ ፕሬዝዳንት በሽር አል አሳድ መንግሥት የተራረፉ ማናቸውም የኬሚካል ጦር መሳሪያ ዐይነቶችን ፈልጎ እንዲያወድም ይሻሉ።

ሦሪያ በጎረቤቶቿ ላይ ስጋት የማትደቅን እና ጊዜያዊው አመራሯም ከአክራሪ ቡድኖች ጋራ ያለውን ግንኙነት እንዲያቋርጥ የሚፈልጉ መሆናቸውን ብሊንከን ተናግረዋል።

በተለይም እስላማዊውን አሸባሪ ቡድን - አይሲስን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚደረገውን ጥረት መቀጠል አስፈላጊ መሆኑንም ሁለቱ ባለ ሥልጣናት ጨምረው ገልጸዋል።

የሦሪያው እስላማዊ አማጺ ቡድን ባደረሰው ብርቱ ጥቃት ለ54 አመታት የዘለቀው የአሳድ ቤተሰብ የጭቆና አገዛዝ ማብቃት የፈጠረውን ሁኔታ ተከትሎ ወደ መካከለኛው ምስራቅ ያቀኑት ብሊንከን፤ የጉዟቸው ሁለተኛ መዳረሻ ካደረጓት አንካራ ላይ ፊዳንን አግኝተው ከማነጋገራቸው አስቀድሞ፤ ትላንት ሃሙስ ከቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶጋን ጋር መነጋገራቸው ታውቋል።

ብሊንከን ዮርዳኖስ ላይም ከንጉስ አብዱላህ ሁለተኛ ቢን አል-ሁሴን እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር አይማን ሳፋዲ ጋር ተገናኝተው ተነጋግረዋል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG