በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በኮንጎ ዲ.ሪ. አማጺያን 24 ሲቪሎችን ገደሉ


ፎቶ ፋይል፦ ኪንሻሳ፤ ኮንጎ
ፎቶ ፋይል፦ ኪንሻሳ፤ ኮንጎ

"ኅብረት ለኮንጎ ልማት" ወይም በምጻረ ቃሎ "ኮዴኮ" የተሰኘው የአማጺ ቡድን በሣምንቱ መጨረሻ በምሥራቅ ኮንጎ ዲ.ሪ. 24 ሲቪሎችን ሳይገድል አይቀርም ሲል ኤኤፍፒ የዜና ወኪል የአካባቢውን ሰዎች ጠቅሶ ዘግቧል።

ጥቃቱ ጁጉ በተባለው ግዛት ባለፈው እሁድ መፈጸሙን በአካባቢው የሲቪል ማኅበረስብ መሪ የሆኑት ቻሪት ባንዛ ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

ባንዛ እንዳሉት የኮዴኮ ተዋጊዎች በሦስት መንደሮች የሚገኙ ቤቶችን በእሳት አጋይተው 24 ሰዎችን ገድለዋል። መድረስ ያልቻሏቸው መንደሮች በመኖራቸው የሟቾቹ ቁጥር ከዚህም ሊጨምር እንደሚችል የሲቪል ማኅበረስብ መሪው ተናግረዋል።

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአካባቢው የረድኤት ሠራተኛ ጥቃቱ እንደተፈጸመ ወዲያውኑ 16 አስከሬኖች መገኘታቸውን ተናግረዋል።

የሟቾቹን ቁጥር በራሱ ማረጋገጥ እንዳልቻለ ኤኤፍፒ በሪፖርቱ ጠቁሟል።

የኮዴኮ ተዋጊዎች ጥቃቱን የፈጸሙት የእነርሱ ጎሳ አባል የሆነ አንድ መምህር በመገደሉ ምክንያት በበቀል ተነሳስተው ሳይሆን አይቀርም ሲሉ በአካባቢው የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪ ተናግረዋል።

ኮዴኮና ሌሎች በደርዘን የሚቆጠሩ በምሥራቅ ኮንጎ የሚገኙ አማጺያን በቅርቡ በኬንያ የሰላም ውይይት አድርገው እንደነበር ይታወሳል።

XS
SM
MD
LG