ዋሺንግተን ዲሲ —
ምስራቃዊ ኮንጎ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ውስጥ ተጠርጣሪ ታጣቂዎች ቢያንስ አስራ ዘጠኝ ሰዎችን መግደላቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ተናገሩ።
ባለሥልጣናቱ እንዳሉት ሰሜን ኪቩ ክፍለ ሀገር በሚገኘው ቪሩንጋ የዱር አራዊት ፓርክ አካባቢ የሚገኘውን መንደሩን የወረሩት ታጣቂዎቹ በመኖሪያ ቤቶቹ የንብረት ዝርፊያ ፈጽመዋል፥ ቤቶች አቃጥለዋል።
የወረዳው የሰብዓዊ መብቶች ቡድን መሪ በሰጡት ቃል ይህን ተግባር የፈጸመው የተባበሩት ዲሞክራሲያው ኃይሎች በሚል ስም የሚጠራው እስላማዊ ታጣቂ ቡድን መሆኑን ተናግረዋል። ቡድኑ በቅርብ ዓመታት በሽዎች የተቆጠሩ ሰዎችን በተለይ በገጠሩ አካባቢ በመግደል የተወነጀለ ነው።
ስለጥቃቱ ሃላፊነት የወሰደ ወገን እስካሁን አልተሰማም፥ የኤዲኤፍን ምላሽ ለማግኘት እንዳልተቻለ ሮይተርስ ዘግቧል።