ምሥራቃዊ ኮንጎ ኦይቻ ከተማ ውስጥ በትላትናው ምሽት ተጠርጣሪ እስላማዊ ጽንፈኞች ባደረሱት ጥቃት 26 ሰዎች መገደላቸውን ከንቲባው ትላንት አስታወቁ።
ግድያውን የፈጸመው በምስራቅ ኮንጎ የሚንቀሳቀሰው የዓለም አቀፉ እስላማዊ ጽንፈኛ ቡድን ‘አይሲስ’ አጋር መሆኑን ይፋ ያደረገውና በተደጋጋሚም ጥቃቶችን የፈጸመው ራሱን የተባበሩት ዲሞክራሲያዊ ኃይሎች ብሎ የሚጠራው (በእንግሊዝኛው ምሕጻረ ቃል ADF የተባለው) የዩጋንዳው ታጣቂ ቡድን መኾኑን ከንቲባው አክለው ተናግረዋል።
ጥቃቱ የተፈፀመው በአገሬው የሰዓት አቆጣጠር ትላንት ከምሽቱ 5 ሰዓት አካባቢ ላይ መሆኑንም ሰሜን ኪቩ ግዛት ውስጥ የምትገኘው የኦይቻ ከተማ ከንቲባ ኒኮላስ ኪኩኩ ተናግረዋል። በጥቃቱ የቆሰሉ አራት ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸውን ጨምረው ገልጠዋል።
"ያለ ምንም ማስጠንቀቂያ የተፈጸመ መሆኑ በጣም ያሳዝናል" ያሉት የአካባቢው የመብት ተሟጋች ሃቪየር ካሴሬካ ካሳዪሪዮ በበኩላቸው፣ ጥቃቱን የፈጸመው ADF መሆኑን አረጋግጠዋል።
ዩጋንዳ እና ኮንጎ ሸማቂዎቹን ‘ከሥራቸው ለመንቀል’ ከዛሬ ሁለት አመት በፊት የጋራ ወታደራዊ ዘመቻ አካሂደዋል። የዩጋንዳ ጦር ባለፈው ወር ከ560 በላይ ተዋጊዎችን መግደሉን እና ከወታደራዊ ካምፖቻቸው የተወሰኑትን ማውደም መቻሉን ማስታወቁ ይታወሳል።
መድረክ / ፎረም