የዩናይትድ ስቴትስ ቴክሳስ ክፍለ ግዛት በኦስተን ከተማ ትናንት ማክሰኞ በተከታታይ በተፈጸሙ የተኩስ ጥቃቶች አራት ሰዎች መሞታቸውን እና ቢያንስ ሶስት መቁሰላቸውን አስታወቁ፡፡
በነዚህ ጥቃቶች እና ሳን አንቶኒዮ ከተማ አቅራቢያ በሞቱ ሌሎች ሁለት ሰዎች ግድያ የተጠረጠረ ሰው በቁጥጥር ስር መዋሉ ተገልጿል፡፡
የግድያዎቹ ሰለባዎች አስከሬኖች ኦስቲን ከተማ በሚገኙ ሁለት መኖሪያ ቤቶች እና ከሳን አንቶኒዮ በስተምስራቅ በሚገኝ መኖሪያ ቤት ውስጥ ተገኝተዋል፡፡ በጥቃቱ የቆሰሉት ሁለት ፖሊሶች እና አንድ ብስክሌት እየነዳ የነበረ ሰው መሆናቸውን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በ30ዎች እድሜ ውስጥ የሚገኘው ስሙ ያልተገለጸው ተጠርጣሪ በግድያ ወንጀል ክስ የተመሰረተበት መሆኑንም ፖሊስ ተናግሯል፡፡
አሶሲየትድ ፕሬስ እንደዘገበው ግድያውን ፈጽሟል በተባለው ተጠርጣሪና በጥቃቱ ሰለባዎች መካከል አንዳች ግንኙነት ስለመኖሩ ወዲያውኑ አልታወቀም፡፡
ሌሎቹ ሁለቱ ሰዎች ከኦስተኑ ግድያ በፊት ሳን አንቶኒዮ በስተምስራቅ ቤክሳር ወረዳ ተገድለዋል ተብሎ እንደሚታመን ባለስልጣናት ተናግረዋል
በመኪናው ከፖሊስ ሊያመልጥ የሞከረው ተጠርጣሪ ከምሽቱ አንድ ሰዓት ከሩብ ላይ መኪናውን አውራ ጎዳና ላይ ሲያሽከርከር በመጋጨቱ ምንም ጉዳት ሳይደርስበት በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
መድረክ / ፎረም