በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሶማሊያ አጥፍቶ ጠፊ ባደረሰው ጥቃት ቢያንስ 20 ሰዎች ሞቱ


በሶማሊያ፣ አንድ አጥፍቶ ጠፊ፣ ዛሬ ማለዳ፣ በአንድ ወታደራዊ አካዳሚ ላይ አድርሶታል፤ በተባለ ጥቃት፣ ቢያንስ 20 የሚደርሱ የሶማልያ ወታደሮች እንደ ሞቱ፣ የቪኦኤ ምንጮች ተናግረዋል።

ጥቃቱ የተፈጸመው፣ ጃሊ ሲያድ በተባለው ወታደራዊ አካዳሚ ውስጥ የሚገኙ ወታደሮች፣ ከቁርስ በኋላ ተሰልፈው ሳለ ነው፤ ተብሏል።

በጉዳዩ ላይ እንዲናገሩ ፈቃድ እንዳልተሰጣቸው የገለጹና ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ ወታደራዊ ባለሥልጣን ለቪኦኤ እንደተናገሩት፣ በጥቃቱ፣ በደርዘን የሚቆጠሩ ወታደሮችም ተጎድተዋል። አንዳንዶቹም፣ ለሕይወት በሚያሰጉ ኹኔታዎች ውስጥ እንደሚገኙ፣ ምንጩ ጨምረው ገልጸዋል።

አል-ሻባብ ለጥቃቱ ሓላፊነት እንደሚወስድ፣ በቴሌግራም መልዕክት አስታውቋል። አጥፍቶ ጠፊ አባሉ፣ 73 የሚደርሱ ወታደሮችን እንደ ገደለ እና 124ቱን ደግሞ እንደ አቆሰለ ቡድኑ ቢገልጽም፣ የሟቾቹ እና የተጎጂዎቹ ብዛት በገለልተኛ ወገን አልተረጋገጠም።

ጥቃት አድራሹ አጥፍቶ ጠፊ፣ ወታደራዊ ልብስ ለብሶ እንደነበርም ታውቋል።

የጥቃቱ ዒላማ የኾነው ብርጌድ፣ በአፍሪካ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን ማለትም 600 ሰዎችን የገደለው እ.እ.አ. የ2017 የሞቃዲሹ የሽብር ጥቃት ሰለባዎችን ለማሰብ የተቋቋመ ብርጌድ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG