በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ፕሬዚዳንት ሃሰን ኦማር አል በሺር ኳታር ገቡ


የሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሃሰን ኦማር አል በሺር ለታወከች ሃገራቸው ዕርዳታ ፍለጋ ትላንት ኳታር ነበሩ። ጉብኝቱን ያደረጉት ባለፉት አራት ሣምንታት መንግሥታቸውን በመቃወም ሰልፍ የወጡ ዜጎች መገደል፣ መጎዳትና መታሠር እንዳሳሰባት ዩናይትድ ስቴትስ እየገለፀች ባለችበት ወቅት ነው።

በሺርና የኳታሩ መሪ ሼህ ታሚም ቢን ሐማድ አል ታኒ ትላንት ዶሃ ከተማ በተገናኙበት ወቅት፣ በጦርነት የተበታተከችውን ዳርፉርን ጨምሮ በበርካታ ርዕሶች ላይ ተወያይተዋል ሲል የኳታር ዜና አገልግሎት ዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በካርቱም የተባበሩት የአረብ ኤሚሬቶች ሩሲያና ቱርክ ለሱዳን ዕርዳታ ለመስጠት ያቀረቡትን ሃሳብ - ሃገራቸው መቀበሏን የነዳጅ ዘይት ሚኒስትሩ አዛሪ አብድል ቃድር አስታውቀዋል።

ሃገራቱ ምን ያህል ዕርዳታ ለመስጠት ቃል እንደገቡና መቼ እንደሚደርስ ግን ሚኒስትሩ በግልፅ አላሳወቁም።

በሌላ በኩል ባለፉት አራት ሣምንታት ሱዳን ውስጥ በተካሄዱ ፀረ መንግሥት ሰልፎች ብዛት ያላቸው ሰዎች እየተያዙ መታሠራቸው እንዳሳሰበው የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤት በትላንትናው ዕለት አስታውቋል።

የሱዳን ሕዝብ በሃገሪቱ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ለውጦች እንዲደረጉ በሰላማዊ መንገድ የሚያቀርበውን ጥሪ እንደግፋለን ሲል የዩናይትድ ስቴትስ ውጭ ጉዳይ መ/ቤት ቃል አቀባይ በመግለጫው አክሏል።

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG