በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳናውያን የፈጥኖ ደራሽ ወታደሮች በነጭ አባይ ግዛት በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎችን ገደሉ


ነጭ አባይ ግዛት፣ ሱዳን
ነጭ አባይ ግዛት፣ ሱዳን

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል በነጭ አባይ ግዛት በፈጸመው ጥቃት ጨቅላ ህፃናትን ጨምሮ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሲቪሎች መሞታቸውን የሱዳን ባለሥልጣናት እና የመብት ተሟጋች ድርጅቶች ትላንት ማክሰኞ አስታወቁ።

የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ፣ “ቡድኑ ባለፉት ጥቂት ቀናት ውስጥ በሱዳን ጦር ‘አሰቃቂ ሽንፈት’ ከደረሰበት በኋላ በአል-ጊታይና አካባቢ በሚገኙ መንደሮች ውስጥ በሰላማዊ ሰዎች ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ፈጽሟል።” ብሏል፡፡ የሱዳን ዶክተሮች ሠራተኛ ማኅበር የሟቾች ቁጥር 300 መኾኑን ሲያስታውቅ መግለጫው ቁጥሩ 433 አድርሶታል።

በሲቪሎች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶችን የሚከታተለው የአደጋ ጊዜ ጠበቆች የመብት ተሟጋች ቡድን ትላንት ማክሰኞ ማለዳ በሰጠው መግለጫ፣ “ባለፉት ሦስት ቀናት ውስጥ፣ ሴቶች እና ህፃናትን ጨምሮ ከ200 በላይ ሰዎች በፈጥኖ ደራሽ ጥቃቶች መገደላቸውን” ጠቅሶ ሌሎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቆስለዋል ብሏል።

“ጥቃቶቹ ግድያ፣ አፈና፣ በግዳጅ መሰወር፣ ዝርፊያ እና ለማምለጥ የሚሞክሩት ላይ ጥይት መተኮስ ይገኙበታል” ሲል ቡድኑ ገልጿል።

የባህል እና ማስታወቂያ ሚኒስትር ካሊድ ዓሊ አሌይሲር ፌስቡክ ላይ እንደተናገሩት፣ በነጭ አባይ ግዛት ውስጥ፣ በአልቃዳሪስ እና በአል ኻልዋት መንደሮች የተፈጸሙት የቅርብ ጊዜዎቹ የፈጥኖ ደራሽ ጥቃቶች "መከላከያ በሌላቸው ሰላማዊ ዜጎች ላይ የተፈጸሙ ስልታዊ ጥቃቶች ናቸው”ብሏል።

የሱዳን ጦር ባላፈው ቅዳሜ በነጭ አባይ ግዛት “ተጨማሪ ከተሞችን እና መንደሮችን ነፃ አውጥቻለሁ”ብሏል። እኤአ ከመጋቢት 2023 ዓ.ም ጀምሮ ሀገሪቱን ለመቆጣጠር ሲታገል ለነበረው ተቀናቃኙ የፈጥኖ ደራሽ ቡድን ወሳኝ የአቅርቦት መንገዶችን ማቋረጡንም አስታውቋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት እንደሚለው “በሱዳን ያለው ጦርነት ከ24 ሺሕ በላይ ሰዎችን የገደለ ሲሆን፣ ከ14 ሚሊዮን በላይ ወይም 30 ከመቶ የሚኾነውን ሕዝብ ከመኖሪያ ቀያቸው አፈናቅሏል።” ወደ 3.2 ሚሊዮን የሚገመቱ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ሸሽተዋል።

የመንግሥታቱ ድርጅት ትላንት ማክሰኞ እንዳስታወቀው እንደ አውሮፓውያን አቆጣጠር በ2024 የሰብአዊ መብት ቢሮው ከ4 ሺሕ 200 በላይ የዜጎች ግድያዎችን መዝግቧል፣ አጠቃላይ ቁጥሩም ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችል ገልጿል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት፣ ከትላንት በስቲያ ሰኞ በሀገሪቱ 21 ሚሊየን ለሚኾኑ ዜጎች እና ጦርነቱን ወደ ውጭ ለሸሹ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎችን ለመርዳት እኤአ ለ2025 የሱዳን ሰብአዊ ምላሽ፣ 6 ቢሊዮን ዶላር ተማጽኗል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የርዳታ ኃላፊ ቶም ፍሌቸር በመግለጫቸው "ይህ በመጠን እና በወሳኝነቱ ታይቶ የማይታወቅ ሰብአዊ ቀውስ ነው" በመሆኑም “በመጠን እና በአስፈላጊነቱ ከእስከዛሬው የተለየ ምላሽ ይፈልጋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የኖርዌይ የዓለም አቀፍ ልማት ሚኒስትር አስመንድ ኦክሩስት በሰላማዊ ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጥቃት እና በደል መባባሱን አውግዘዋል።

“በሱዳን በተባባሰው ግጭት ሳቢያ የዜጎች ሞት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩ በጣም ያሳስበኛል፣ በሲቪሎች እና በሲቪል መሰረተ ልማቶች ላይ የሚፈጸሙ ዘግናኝ ጥቃቶች አስመልከተው የሚወጡ ሪፖርቶች አስደንግጠውኛል፣ እንዲህ ዐይነት ጥቃቶች በአስቸኳይ መቆም አለባቸው።” ሲሉ ኦክረስት በኖርዌይ መንግሥት ዋና የመረጃ አውታውር ድረ ገጽ ላይ አስፍረዋል፡፡

የፈጥኖ ደራሽ ጦር የገዚራ ግዛት ዋና ከተማ የሆነችውን ዋድ ሜዳኒ እና ሌሎችም የግዛቲቱ አካባቢዎችን መቆጣጠር የተሳነው በመሆኑ ከፍተኛ ሽንፈት ሲደርስበት ወታደራዊ ቡድኑ ከፍተኛ የበላይነት እንዲይዝ አድርጎታል፡፡ የሱዳን ጦርም የሀገሪቱን ትልቁን የነዳጅ ማጣሪያ ፋብሪካ እንደገና መቆጣጠር ችሏል።

የፈጥኖ ደራሽ ጦር የታላቋ ካርቱምን አካባቢን፣ የኦምዱርማን እና የካርቱም ባሕሪ ከተሞችን መቆጣጠር ያቃተው ይመስላል።

“ፈጥኖ ደራሹ ጦር እና ወኪሎቹ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየፈጸሙ ነው” የሚለውን የአሜሪካ ግምገማን ጨምሮ፣ ጦርነቱን ለማስቆም ዓለም አቀፍ የሽምግልና ሙከራዎች ቢደረጉም ጦርነቱ ፍጻሜ አላሳየም፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG