በኢትዮጵያ ፌደራል ኃይሎች እና በሀገሪቱ ሰሜን ምዕራብ አካባቢ የሚገኙ ታጣቂዎች መካከል የሚካሄደው ግጭት፣ የሀገራቸውን ግጭት የሸሹ ሱዳናዊያን ስደተኞችን 'ለከፍተኛ አደጋ' ማጋለጡን ሂዩማን ራይትስ ዋች ዛሬ ሐሙስ ባወጣው ሪፖርቱ አስጠንቅቋል።
የኢትዮጵያ መንግሥት የፋኖ ታጣቂዎች በሚንቀሳቀሱበት የአማራ ክልል ላይ ጥሎት የነበረው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በሰኔ ወር ቢያበቃም፣ ግጭቱ እንደቀጠለ ሲሆን ከመስከረም ወር ጀምሮም ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፌደራል ኃይል በክልሉ ተሰማርቷል።
ክልሉ ከሱዳን ጋር የሚዋሰን ሲሆን፣ በሱዳንም ከእ.አ.አ ከ2023 ጀምሮ በፈጥኖ ደራሹ ኃይሎች እና በገዢው መሪ አብዱልፈታህ አልቡርሃን መካከል በሚካሄደው የእርስ በእርስ ጦርነት በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አካባቢያቸውን ጥለው ተሰደዋል።
የሂዩማን ራይትስ ዋች ምክትል የአፍሪካ ዳይሬክተር ላቲሺያ ባደር ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ በሰጡት አስተያየት "በኢትዮጵያ የሚገኙ የሱዳን ስደተኞች ከአንድ አመት በላይ በተለያዩ ታጣቂ ቡድኖች ጥቃት ሲደርስባቸው ቆይቷል" ብለዋል።
"እነዚህ ስደተኞች ሀገራቸው የደረሰባቸውን አሰቃቂ በደል ሸሽተው የተሰደዱ አንደመሆናቸው በአጣዳፊነት የሚያስፈልጋቸው የደህንነት ጥበቃ እንጂ ለህይወታቸው ተጨማሪ ስጋት አይደለም" ብለዋል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ባወጣው ሪፖርት በሁለት መጠለያ ጣቢያዎች አቅራቢያ "ታጣቂዎች እና የአካባቢው ሚሊሺያ ግድያ፣ ድብደባ፣ ዝርፊያ፣ እገታ እና አስገዳጅ የጉልበት ስራ ፈፅሟል" ብሏል። የመብት ቡድኑ አክሎ የኢትዮጵያ መንግሥት መጠለያዎቹን ግጭት ባለባቸው አካባቢ ማቋቋሙን እና በቂ ጥበቃ አለማድረጉን በመግለፅ ከሷል።
ሂዩማን ራይትስ ዋች ሪፖርቱ ያካተታቸውን ግኝቶች ለኢትዮጵያ የስደተኞች አገልግሎት ማጋራቱን የገለጸ ሲሆን፣ አገልግሎቱ መጠለያዎቹ ለግጭት አካባቢ ቅርብ መሆናቸን ሆኖም አስፈላጊው የጸጥታ ጥበቃ እንደሚደረግ መግለፁን አመልክቷል። እየተባባሰ የመጣው የአማራ ክልል ግጭት በሐምሌ ወር የአውላላ እና ኩመር መጠለያ ጣቢያዎች እንዲዘጉ ምክንያት መሆኑንም አክሎ አመልክቷል።
በሂዩማን ራይትስ ዋች ለቀረበው ክስ የኢትዮጲያ መንግሥትን ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም፡፡
መድረክ / ፎረም