በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ "ግብፅ የአየር ጥቃት ፈጽማብኛለች" አሉ


የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ)
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ)

የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ጦር መሪ መሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ (ሄሜቲ) "ግብፅ በወታደሮቻችን ላይ የአየር ድብደባ ትፈጽማለች፣ ለሱዳን ጦርም ሥልጠናና ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ትሰጣለች" ሲሉ ከሰዋል፡፡

የግብፅ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ትላንት ባወጣው መግለጫ ሄሚቲ ትላንት ረቡዕ ባሰሙት ንግግር ያሰሙትን ክስ በማስተባበል “ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሄሜቲ የቀረበው ክስ የእውነት ስለመሆኑ ማስረጃ መኖሩን እንዲያጣራም” አሳስቧል፡፡

ሄሚቲ “ግብጽ ለሱዳን ጦር ድጋፍ እየሰጠች ነው” በማለት የከሰሱት፣ ለ18 ወራት ያህል በዘለቀው ጦርነት የሱዳን ጦር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የበላይነት እያገኘ መጥቷል በተባለበት በዚህ ወቅት መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ግብፅ የሱዳኑ ጦር መሪ ጀኔራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃን የቅርብ ወዳጅ ተደርጋ ብትታይም ግጭቱን ለመሸምገል ጥረት ከሚያደርጉት ከዩናይትድ ስቴትስ እና ሳኡዲ አረብያ ጋር አብራ ሰርታለች፡፡ ካይሮ የተቀናቃኞቹን ወገኖች ውይይት በዚህ ዓመት መጀመሪያ ላይ አስተናግዳለች፡፡

ሄሚቲ በቪዲዮ በተቀረጸ መልዕክታቸው “በዚህ ግጭት ግብፅ በፈጸመችው የአየር ጥቃት የአሜሪካ ቦምቦችን ተጠቅማለች” ብለዋል፡፡

“አሜሪካውያኑ ባይስማሙ እነዚህ ቦምቦች ሱዳን አይደርሱም ነበር” ሲሉም ሄሚቲ አክለዋል፡፡

“ሀገሪቱ ውስጥ የትግራይ፣ የኤርትራ፣ የአዘርባይጃን እና ዩክሬን ቅጥር ነፍሰ ገዳዮች ታይተዋል” ያሉት ሄሚቲ “ኢራናውያን ከሱዳን ጦር ጎን በመሆን በጦርነቱ ተሳትፈዋል” የሚለውን ክስ በድጋሚ አሰምተዋል፡፡

የሱዳን ጦር በቅርቡ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም እና በደቡብ ምስራቅ ግዛት ጀብል ሞያ አካባቢ ድል ቀንቶታል፡፡ ጀብል ሞያ ሄሚቲ ወታደሮቻቸው ከስትራቴጂያዊ አካባቢ ተገፍተው እንዲወጡ ግብጽ የአየር ጥቃት ፈጽማለች ያሉበት አካባቢ ነው፡፡

ቀደም ሲል የታየውን የሰላም ፍላጎት ድምጸት በሚለወጥ መልኩ የፈጥኖ ደራሹ ጦር መሪ ባሰሙት ንግግር “ ይህ ጦርነት በአንድ ወይም በሁለት ሶስት እና አራት ዓመታት ውስጥ አያልቅም፡፡ አንዳንዶች ስለ አንድ ሚሊዮን ወታደር ያወራሉ በቅርቡ አንድ ሚሊዮን እንገባለን” ብለዋል፡፡

እኤአ በመጋቢት 2023 የጀመረው የሱዳን ጦርነት ወደ 10 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎችን ከቤት ንብረታቸው አፈናቅሏል፣ ረሀብን በከፍተኛ ደረጃ አስፋፍቷል፥ በአብዛኛው ፈጥኖ ደራሹ ጦር ተጠያቂ ነው የሚባልበትን ብሄር ተኮር የሆኑ ጥቃቶች እንዳስነሳ የሮይተርስ ዘገባ አመልክቷል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG