በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የዓለም የምግብ ፕሮራም በሱዳን ርዳታ ለማድረስ መቸገሩን አስታወቀ


ግጭቱን ሸሽተው ቻድ የገቡ የሱዳን ስደተኞች በቻድ የዕርዳታ እህል ሲቀርብላቸው
ግጭቱን ሸሽተው ቻድ የገቡ የሱዳን ስደተኞች በቻድ የዕርዳታ እህል ሲቀርብላቸው

የዓለም የምግብ ፕሮግራም፣ በሱዳን መዲና ካርቱም እና በሌሎችም አካባቢዎች፣ በሁለቱ ተፋላሚ የጦር ጀነራሎች መካከል ከባድ ውጊያ በቀጠለበት ኹኔታ ርዳታ ለማድረስ መቸገሩን፣ ትላንት አስታውቋል። ተፋላሚ ኃይሎች ለተራድኦ ወኪሎች የደኅንነት ዋስትና እንዲሰጡ ጥሪ አቅርቧል። በርካታ የተኩስ ማቆም ስምምነቶች ተግባራዊ ሳይኾኑ ቀርተዋል።

በሱዳን የዓለሙ የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ ሌኒ ኪንዝሊ እንዳሉት፣ ጦርነቱን ሸሽተው አንጻራዊ ሰላም ወዳሉባቸው አካባቢዎች ለተጠለሉ ሰዎች ምግብ በማደል ላይ መኾናቸውን ተናግረዋል።

ኪንዝሊ ከሚገኙበት ጀርመን ለቪኦኤ በላኩት የጽሑፍ መልዕክት፣ ፕሮግራሙ ለ384ሺሕ ሰዎች የምግብ ርዳታ ለማድረስ ዕቅድ መያዙን አስታውቀዋል። በዚኽም መሠረት ወደ ከሰላ፣ ገዳሪፍ እና ነጭ ዓባይ ክልል እንደሚላክ አስታውቀዋል።

ቃል አቀባዩ አክለው እንዳሉት፣ በከፋ መልኩ እየተካሔደ ባለው ውጊያ ምክንያት፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች በሕይወት ለመቆየት በሚጥሩባቸው አካባቢዎች ርዳታ ለማድረስ አስቸጋሪ ኾኗል።

በሱዳን እየተፋለሙ ያሉት የአገሪቱ ሠራዊት እና የፈጥኖ ደራሽ ድጋፍ ሰጪ ኃይል መሪዎች የኾኑት ሁለት ተቀናቃኝ ጀነራሎች፣ ተኩስ ለማቆም በተደጋጋሚ ቢስማሙም ተግባራዊ ሳያደርጉት ውጊያውን ቀጥለዋል።

የዓለሙ የምግብ ፕሮግራም ቃል አቀባይ፣ ሁለቱ ተዋጊዎች፥ ለረድኤት ወኪሎች የደኅንነት ዋስትና ሰጥተው ርዳታ እንዲደርስ እንዲያደርጉ ጥሪ አድርገዋል።

ከሦስት ሳምንታት በፊት በጀመረው ውጊያ ምክንያት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሲሞቱ፣ እንደ ተመድ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን መረጃ፣ 128 ሺሕ ሰዎች ሱዳንን ለቀው ወጥተዋል። በሚቀጥሉት ሳምንታት፣ 900 ሺሕ የሚኾኑ ሱዳናውያን ወደ ጎረቤት አገሮች ሊሰደዱ እንደሚችሉ፣ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽኑ አመልክቷል።

XS
SM
MD
LG