በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሱዳን የ72 ሰዓታት ተኩስ አቁሙ በመከበር ላይ ነው


ፎቶ ፋይል፡ ካርቱም፣ ሱዳን
ፎቶ ፋይል፡ ካርቱም፣ ሱዳን

አገሪቱን ለመርዳት ዓለም አቀፍ ጉባኤ በመካሔድ ላይ ነው

በሱዳን፣ ትላንት እሑድ ማለዳ የጀመረው፣ የ72 ሰዓታት ተኩስ ማቆም የያዘ በመሰለበት በዛሬው ዕለት፣ ዓለም አቀፍ ለጋሾች፣ አገሪቱን በሚረዱበት ሁኔታ ላይ ለመነጋገር፣ ጀኒቫ ላይ ጉባኤ ተቀምጠዋል።

ከሁለት ወራት በላይ የዘለቀው ጦርነት፣ ከፍተኛ ቀውስ እንዳስከተለ፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በመግለጽ ላይ ነው።

የአየር ጥቃትም ሆነ የሌላ መሣሪያ ድምፅ ሳይሰሙ መዋላቸውን፣ በርካታ የካርቱም ነዋሪዎች፣ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል። ይኸው የተኩስ አቁም ጋብታ፣ በሕክምና፣ በመብራት፣ በውኃ እና በሌሎችም መሠረታዊ አቅርቦቶች ችግር ለሚሠቃዩት ሱዳናውያን፣ መጠነኛ እፎይታ ሰጥቷል፤ ተብሏል።

ሚያዝያ 7 ቀን የጀመረውና ከሁለት ወራት በላይ የቆየው ግጭት፣ ከሁለት ሺሕ በላይ ሰዎችን ሕይወት ሲቀጥፍ፣ ከ528ሺሕ በላይ የሚኾኑትን ወደ ጎረቤት አገራት እንዲሸሹ አድርጓል። ከ2ነጥብ2 ሚሊዮን በላይ የሚኾኑቱ ደግሞ፣ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ተመድ እንደሚለው፣ ከ25 ሚሊዮን በላይ እንደሚደርስ የሚገመተው ሱዳናዊ፣ ሰብአዊ ርዳታ ጠባቂ ነው፡፡ ይኸውም፣ ከግማሽ በላይ የሚኾነው የአገሪቱ ሕዝብ፣ እስከ አሁን የሚደርሰው ርዳታ እጅግ ጥቂት ነው።

ጀኒቫ ላይ፣ ዛሬ ይጀመራል የተባለው ጉባኤ፣ ለሱዳንም ሆነ ለአካባቢው ሀገራት የሚያስፈልገውን ርዳታ በተመለከተ ይነጋገራል፤ ተብሏል። በጉባኤው ላይ፣ ከተመድ በተጨማሪ፡- ግብጽ፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ካጠር እና የአፍሪካ ኅብረት እንደሚሳተፉበት ታውቋል።

XS
SM
MD
LG