በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን አየር ኃይል ተዋጊ ጄት በፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ተመትቶ መውደቁ ተሰማ


ፎቶ ፋይል፦ ካርቱም፤ ሱዳን
ፎቶ ፋይል፦ ካርቱም፤ ሱዳን

በሱዳን ዋና መዲና ካርቱም፣ ዛሬ ማክሰኞ፣ በከባድ መሣሪያ የታገዘ ከፍተኛ ውጊያ በበርካታ መንደሮች እንደተደረገ ሲገለጽ፣ አንድ ተዋጊ ጄት ተመትቶ ሲወድቅ እንደተመለከቱ፣ የዐይን ምስክሮች፣ ለኤኤፍፒ ዜና ወኪል ተናግረዋል።

“ጄቱ ወደ መሬት ሲወድቅ፣ አብራሪዎቹ በጃንጥላ ሲወርዱ አይተናል፤” ሲል፣ እንደ ሌሎቹ ምስክሮች ኹሉ ስለ ደኅንነቱ ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ፣ አንድ የሰሜን ካርቱም ነዋሪ ለኤኤፍፒ ተናግሯል።

ተዋጊ ጄቱን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ መትቶ እንደጣለ፣ አንድ በልዩ ኃይሉ ውስጥ ያሉ ምንጭ፣ ለዜና ወኪሉ ተናግረዋል።

የተዋጊ ጄት አብራሪው፣ በፓራሹት ከወረደ በኋላ በቁጥጥር ሥር እንዳዋለው ጨምሮ የገለጸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፣ የሱዳን አየር ኃይልን፥ “እልቂት ፈጽሟል፤” ሲል ወጅሏል።

ከወንዙ ማዶ ባለችው ኦምዱርማን፣ በተለያዩ መሣሪያዎች የታገዙ ከባድ ውጊያዎች እንደተካሔዱ፣ አንድ የዐይን ምስክር ተናግሯል።

ሌሎች ምስክሮች ደግሞ፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ፥ ሰሞኑን ጥቃት በፈጸመበት ብሔራዊ የቴሌቭዥን ጣቢያው ሕንጻ ባለበት አካባቢ፣ የአየር ጥቃት እና የፀረ አውሮፕላን ተኩሶች እንደሰሙ ተናግረዋል።

XS
SM
MD
LG