በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሱዳን ውስጥ የህዝባዊ ዕምቢተኝነት እና አድማ እየተካሄደ ነው


የህዝባዊ ዕምቢተኝነት እና አድማ ሱዳን ካርቱም ትናንት ተጀምሯል
የህዝባዊ ዕምቢተኝነት እና አድማ ሱዳን ካርቱም ትናንት ተጀምሯል

የሱዳን አፍቃሪ ዲሞክራሲ ቡድኖች ወታዳራዊ የመንግሥት ግልበጣውን በመቃወም የጠሩት የሁለት ቀን የህዝባዊ ዕምቢተኝነት እና አድማ ትናንት ተጀምሯል።

የኢንተርኔት እና የስልክ አገልግሎቶች መቋረጡን የቀጠለ በመሆኑ የተቃውሞው ተሳታፌዎች ቁጥር ብዛት እንዳልነበረው ሮይተር ዘግቧል።

ወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣውን ለማስቀልበስ የታለመውን የአድማ ጥሪ የመሩት ከሁለት ዓመታት በፊት የቀድሞውን አምባገነን ኦማር አልበሽርን ከሥልጣን ያስወገደውን ተቃውሞ ያስተባበረው የሱዳን ባለሙያዎች ማህበር እና የተለያዩ ሃገር ውስጥ ያሉ ተቃዋሚ ቡድኖች መሆናቸው ተገልጿል።

ብዛት ያላቸው የመንግሥት ግልበጣው ተቃዋሚ መምህራን ዋና ከተማዋ ካርቱም የትምህርት ሚኒስቴሩ ደጃፍ ወታደራዊ አስተዳደር አንፈልግም የሚሉ ሰሌዳዎችን ይዘው የወጡ ሲሆን የጸጥታ ሃይሎች አስለቃሽ ጋዝ ረጭተውባቸዋል፥ ሰማኒያ ሰባት ሰዎች መታሰራቸውን የመምህራን ማህበሩ ገልጿል።

ኒያላ እና አትባራን ጨምሮ በሌሎችም ከተሞች የአልበሲር ታማኞች እንደገና መሾማቸውን በመቃወም በመቶዎች የተቆጠሩ ሰዎች ሰልፍ ማካሄዳቸውን የአይን እማኞች ገልጸዋል። እንዳንድ ሆስፒታሎች እና የህክምና ሰራተኞች አድማውን ሲቀላቀሉ መደበኛ ስራቸው ላይ የነበሩም እንዳሉ ተዘግቧል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ የሱዳን የጦር ሰራዊቱ ዋና አዛዥ ጄኔራል አብደልፋታህ አል ቡርሃን ትናንት ከአረብ ሊግ መልዕክተኞች ጋር መነጋገራቸው እና መልዕክተኞቹም የድርድርን እና የዲሞክራሲያዊ ሽግግርን አስፈላጊነት አጽንዖት ሰጥተው እንዳሳሰቧቸው ከጽህፈት ቤታቸው የወጣው መግለጫ አመልክቷል።

ጄኔራል ቡርሃን በበኩላቸው የጦር ሰራዊቱ የህዝቡን ፍላጎት ለማሳካት ቁርጠኛ መሆኑን ለመላክተኞቹ እንደገለጹላቸው መግለጫው ጨመሮ አመልክቷል።

በሌላ በኩል የጦር ሃይሉ ከፖለቲካው እንዲወጣ እየጠየቁ ያሉ የተቃውሞ መሪዎች ድርድርም አይደረግም በሚል ለሚቀጥለው ሳምንት ከተጠራው ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፍ አስቀድሞ ከወዲሁ የሚካሄዱ እንቅስቃሴዎችን ይፋ አደርገዋል።

የሲቪላዊው መንግሥት ግልበጣው እአአ ጥቅምት 25 ቀን ከተከሄደበት ጊዜ ጀምሮ በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቃውሞ ሰልፎች የተካሄዱ ሲሆን በሰልፈኞች ላይ የጸጥታ ሃይሎች የሃይል ርምጃ ወስደዋል፤ ቢያንስ አስራ አራት ሰዎች መገደላቸውን እና ሦስት መቶ የሚሆኑ መቁሰላቸውን ነጻው የሱዳን ዶክተሮች የተባለው ቡድን ገልጿል።

ምዕራባውያን ሃያላን ለሱዳን የሚደረጉ የኢኮኖሚ ድጋፎችን ያቋረጡ ሲሆን ያች ሃገር ወደ ዲሞክራሲያው ሽግግር የማትመለስ ከሆነ ያለባት በብዙ ቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር የውጭ ዕዳ መሰረዝ ጉዳይ ችግር ላይ እንደሚወድቅባት እየተናገሩ ናቸው።

XS
SM
MD
LG