የሱዳን ተፋላሚ ወገኖች ለሦስት ቀናት የሚዘልቅ የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ ደርሰዋል። ሁለቱ ወገኖች ዛሬ ማክሰኞ ሥራ ላይ የዋለው ስምምነት ላይ የደረሱት "ብርቱ የሆነ ድርድር" ከተካሄደ በኋላ መሆኑን ዩናይትድ ስቴትስ አስታውቃለች።
ፍልሚያ ላይ ያሉት የሱዳን የጦር ኅይሎች እና ፈጥኖ ደራሽ ኃይል ስምምነቱን ሊያከብሩ ቃል ገብተዋል።
የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አንተኒ ብሊንክን ባወጡት መግለጫ "ዩናይትድ ስቴትስ ውጊያው በዘላቂነት እንዲገታ ለማገዝ ከክልላዊ እና ዐለም አቀፋዊ አጋሮቿ እንዲሁም ባለድርሻ ከሆኑ የሱዳን ሲቪላዊ አካላት ጋር በተቀናጀ መንገድ ትሰራለች። ውጊያውን በቋሚነት ለማክተም እና ለሰብዐዊ ረድዔት ሥራ አስፈላጊው ሥርዐት እንዲኖር ድርድር መካሄዱን ዳር መድረሱን እና ተግባራዊነቱን የሚከታተል ኮሚቴ እንዲቋቋም ትረዳለች" ብለዋል።
የዩናይትድ ስቴትሱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አክለውም "ሱዳናውያኑ ወገኖች ሀገሪቱን የጋራ ግባቸው ወደሆነው ሲቪላዊ መንግሥት እንዲያሸጋግሩ አብረናቸው እንሰራለን" ብለዋል።
በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥሪያ ቤቶች መሰረት አስራ አንድ ቀናት ባስቆጠረው ውጊያ እስካሁን ቢያንስ 427 ሰዎች ተገድለዋል። ሌሎች ከ3700 የሚበልጡ ሰዎች ቆስለዋል።
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የጸጥታ ምክር ቤት አባላት ተፋላሚዎቹ ወገኖች ውጊያውን እንዲያቆሙ፥ ሥርዐት እንዲያሰፍኑ እና ወደ ዲሞክራሲያዊ ሽግግር ጎዳና እንዲመለሱ ብርቱ ጫና እንዲያሳድሩባቸው የድርጅቱ ዋና ጸሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ ትናንት ሰኞ ጥሪ አቅርበዋል። የጸጥታው ምክር ቤት ዛሬ በሱዳን ጉዳይ ላይ ይነጋገራል።
ጉቴሬዥ አክለው የመንግሥታቱ ድርጅት ሱዳን ውስጥና ከሱዳን ውጭ በብዙ መቶዎች የተቆጠሩ ሠራተኞቹን በጊዜያዊነት በማዘዋወር ላይ እንጂ ሀገሪቱን ጥሎ እየወጣ አይደለም" ሲሉ አስረድተዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ሀገሮች ዲፕሎማቶቻቸውን እና ዜጎቻቸውን ለማስወጣት እየተጣደፉ ናቸው፡፡ በአውሮፕላኖች እና በመኪና አጀብ ዚጎቻቸውን በማስወጣት ላይ ካሉት ሀገሮች መካከል ካናዳ፡ ግብጽ፡ ፈረንሳይ፡ ጀርመን፡ ጣሊያን ስዊድን እና ዩናይትድ ስቴትስ ይገኙባቸዋል፡፡
ጦርነቱ ከሚካሄድባት ከዋና ከተማዋ ከካርቱም የወጡት የዩናይትድ ስቴትስ መንግሥት ሰራተኞች አብዛኞቹ ትናንት ሰኞ ከቀጥር በኋላ ዋሽንግተን ገብተዋል።
የብሪታኒያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርም ዜጎቹን ከካርቱም ወጣ ብሎ በሚገኝ የአውሮፕላን ማረፊያ በኩል ዛሬ ማስወጣት መጀመሩን አስታውቋል።
የቻይና የውጪ ጉዳይ ሚንስቴርም አብዛኞቹን ዜጎቹን ማስወጣቱን ገልጿል።
አንዳንድ ሱዳናውያን በበኩላቸው አደገኛ በሆኑ መንገዶች በመኪናም በአውቶቡስም ከጦርነቱ ለመሸሽ እየሞከሩ ናቸው።