በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን የጦር ሠራዊት የሃምዴቲ ተዋጊዎች እንቅስቃሴ እንዳሰጋው ተናገረ


የሱዳን ጦር ሠራዊት በጀኔራል ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ
የሱዳን ጦር ሠራዊት በጀኔራል ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ

የሱዳን ጦር ሠራዊት በጀኔራል ሞሀመድ ሃምዳን ዳጋሎ የሚመራው ታጣቂ ጦር በሚያሳየው እንቅስቃሴ ግጭት ሊፈጠር ይችላል ሲል አስጠነቀቀ፡፡

ፈጣን ድጋፍ ሰጭ ኃይል የተባለው ልዩ ወታደራዊ ጦር የሚያደርገው እንቅስቃሴ በግልጽ ህግን የጣሰ አድራጎት ነው ሲልም የጦር ኃይሉ አስጠንቅቋል፡፡

በተሰናክለው የዲምክራሲ ሽግግር ዕቅድ ላይ ብዙውን ጊዜ የማይናገረው የሀገሪቱ የጦር ኃይል ባወጣው በዚህ መግለጫው፣ የጄኔራል ዳጋሎ ኃይሎች እንቅስቃሴ እና ሰራዊት የማስፈር ዕርምጃን ኮንኗል፡፡

ከጦር ኃይሎች አመራር ስምምነት ውጭ ቢያንስ ቅንጅት እንኳ ሳይደረግ የተወሰደ እምርጃ በመሆኑ ከቀጠለ ውጥረት እና ክፍፍሉን ሊያያብስ አለመረጋጋትም ሊያስከትል ይችላል ብሏል፡፡

ፈጣን ድጋፍ ሰጪ ኃይል የተባለው መደበኛ ያልሆነ ሠራዊት፣ ከሃያ ዓመታት በፊት በዳርፉሩ ጦርነት ከተሳተፉ ሚሊሺያዎች የተውጣጣ ሲሆን በስፋት የሰብዓዊ መብት ጥሰት በመፈጸም ይወነጀላል፡፡

ቡድኑ እኤእ በ2019 ከመደበኛው የጦር ሰራዊት ጋር በመተባበር የረጅም ጊዜውን መሪ ኦመር አል በሺርን ከስልጣን አስወግደዋል፡፡

የ2021ዱን ሌላኛው መንፈቅለ መንግሥትም ያካሂዱት በጋራ ነው፡፡

በአሁኑ ወቅት በመንግሥት አመራር ስልጣን ላይ ያሉ ሦስት የቀድሞ የሽምቅ ተዋጊ መሪዎች፣ የጦር ሰራዊቱን ጀነራል አብደል ፋታህ አል ቡርሃንን እና ሃምዴቲ በሚል ስምም የሚታወቁትን ጄኔራል ዳጋሎን ለማስታረቅ ያነጋገሯቸው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

“ሁለቱም ሃሳባችንን ተቀብለውናል፡፡ በአገር ወዳድነት ስሜት ከኔ ይቅር ተባብለው የደም መፋሰስን እንዲከላከሉ እና አጠቃላይ አገራዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ እንማጸናለን” ሲሉ ማሊክ አጋር፡ ጂብሪል ኢብራሂም እና ሚኒ ሚናዊ መናገራቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

ዳጋሎ የገዢው ወታደራዊ ምክር ቤት ምክትል ሊቀ መንበር ሲሆኑ ሰሞኑን ግን ከጦር ኃይሉ ገሸሽ ብለው ከሲቪላዊው የፖለቲካ ህብረት ጋር ወደመስማማቱ ማምራታቸው ይነገራል፡፡

የመደበኛው የጦር ሠራዊት እና በዳጋሎ የሚመራው ኃይል ግንኙነት በይበልጥ እየሻከረ በመሄዱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምርጫ እስከሚካሄድ ለሁለት ዓመታት የሚቆይ ሲቪል መር የሽግግር መንግሥት እንዲመሰረት በዓለም አቀፍ አካላት የተደገፈውን ስምምነት የሚፈርሙበት ሥነ ስርዐት ዘግይቷል፡፡ የፈጣን ድጋፍ ሰጭ ኃይል (RSF) ታጣቂዎችን ያሳፈሩ ተሽከርካሪዎች ካርቱም ሲገቡ ማየታቸውን እማኞች ተናግረዋል፡፡

የብሄራዊ ኡማ ፓርቲ መሪ፣ ጡረተኛው የጦር መኮንን ፋዳላላህ በርማ ናስር ሁለቱንም ወገኖች ለንግግር የጋበዙ ሲሆን “ ጥንቃቄ ካላደረግን ሁኔታው ከቁጥጥር ውጪ ሊሆን ይችላል፡፡ በቀጣናው ካሉት ሌሎች ብዙ ሀገሮች ልንማር ይገባል “ ማለታቸውን ሮይተርስ ጠቅሷል፡፡

ሃምዴቲ፣ ከጦር ኃይሉ ጋር ያላስማማቸው ዋናው ጉዳይ፣ “ተዋጊዎቻቸውን ወደ መደበኛው የጦር ሠራዊት የሚያቀላቅሉበትን ቁርጥ ያለ የጊዜ ሰሌዳ ለመስጠት እያንገራገሩ መሆናቸው ነው” ሲሉ ሁለት የጦር ኃይሉ ምንጮች መናገራቸውንም ዘገባው አመልክቷል፡፡

ዳጋሎ ከመደበኛው የጦር ሠራዊት ጋር ፍጥጫ ውስጥ መግባት እንደማይፈልጉ በተደጋጋሚ ሲናገሩ ቆይተዋል፡፡ በልዩ ህግ የሚተዳደረው እና ራሱን የቻለ የዕዝ ሰንሰለት ያለው ሠራዊታቸው ቀደም ብሎ ባወጣው መግለጫ “በሀገሪቱ ዙሪያ የሚታየው የታጣቂዎቻችን እንቅስቃሴ የመደበኛ ስምሪት አካል ነው” ሲል አስረድቷል፡፡

የጄነራል ዳጋሎ ፍላጎት ያሰጋው በወታደራዊ ምክር ቤቱ ሊቀ መንበር በጄኔራል አል ቡርሃን የሚመራው የጦር ሠራዊት በበኩሉ ፣ ካርቱም ላይ ተጨማሪ ወታደሮች በተጠንቀቅ ማስፈሩን ወታደራዊ ምንጮቹ ተናግረዋል፡፡

ጄኔራል ዳጋሎ በብዙ አስር ሺዎች የተቆጠሩ ተዋጊዎች ያሏችው ሲሆን ብዛት ያለው የማዕድን ሀብት ማከማቸታቸውንም ሮይተርስ ዘግቧል፡፡

XS
SM
MD
LG