በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ ወደስልጣን ተመለሱ


የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ
የሱዳን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ

የሱዳን የጦር ኃይል ባለፈው ጥቅምት ወር በመንግሥት ግልበጣ ያስወገዳቸውን ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክን ሲቪላዊ ባለሙያዎችን ያካተተ ካቢኔ እንዲመሩ ዛሬ ዕሁድ ወደስልጣን መልሷቸዋል። ሃምዶክ ላይ የተፈጸመውን ግልበጣ በመቃወም ሱዳን ውስጥ ለሳምንታት የሰው ህይወት የጠፋበት ተቃውሞ ቀስቅሷል።

ትልቁን ኡማ ፓርቲን ጨምሮ በጦር ኃይሉ እና በፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል በተደረሰው ስምምነት መሰረት የመንግሥት ግልበጣውን ተከትሎ የታሰሩ የመንግሥቱ ባለስልጣናት እና የፖለቲካ ሰዎች እንደሚለቀቁ ባለስልጣናቱ ገልጸዋል።

የጦር ሰራዊቱ ያካሄደው የመንግሥት ግልበጣ በዐለም አቀፉ ማህበረሰብ ተነቅፏል። በተቃዋሚ ሰልፈኞች ላይ በጸጥታ ኃይሎች የተፈጸመውን ጥቃት ዩናይትድ ስቴትስ እና አጋሮችዋ እንዲሁም የመንግሥታቱ ድርጅት አውግዘውታል።

ሀምዶክን ወደስልጣን ለመመለስ ስምምነት መደረጉ እንደተሰማ ዋና ከተማዋ ኻርቱም ውስጥ ወደ ቤተ መንግሥቱ ያመሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞችን ለመበተን የጸጥታ ኃይሎች አስለቃሽ ጋዝ ተጠቅመዋል።

ስምምነቱ እንደተፈረመ አንዳንድ ተቃዋሚዎች " ሃምዶክ አብዮቱን ሸጡት" በማለት የተቃውሞ መፈክር አሰምተዋል። ሃምዶክ በበኩላቸው "የተስማማሁት ደም መፋሰሱ እንዲቆም ብዬ ነው፥ የሱዳናውያን ውድ ደም አይፍሰስ፤ የወጣቱን ኃይል ወደልማት እና ግንባታ አቅጣጫ እንምራው " ብለዋል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሱዳን የተቀናጀ ሽግግር ድጋፍ ተልዕኮ የተወሰደው የለውጥ ዕርምጃ እንዳስደሰተው ገልጿል።

ቡድኑ ባወጣው መግለጫ "የህዝቡ መሰረታዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ነጻነት እንዲሁም የመናገርና በሰላማዊ መንገድ መሰባሰብ መብቶች ለማስከበር ህገ መንግሥታዊው ስርዐት መከበር እንዳለበት አጥብቀን እናሳስባለን" ብሏል። በማስከተልም ወገኖቹ የፖለቲካ ሽግግሩ ሰብዕዊ መብቶች እና የህግ የበላይነት በሚከበርበት አሳታፊ መንገድ እንዲጠናቀቅ ያሉት ችግሮች ባስቸኳይ መፍታት ይኖርባቸዋል ሲል አሳስቧል።

ከጦር ሰራዊቱ ጋር በጋራ ስልጣን ላይ የነበረው የሲቪሎች ጥምረት 'ከመንግሥት ገልባጮች" ጋር የሚደረግ ንግግር አንፈልግም የተቃውሞ እንቅስቃሴው መቀጠል አለበት ብሏል። የተቃውሞ ሰልፎች የሚያደራጁ ኮሚቴዎችም ስምምነቱን ውድቅ አድርገዋል።

ጠቅላይ ሚንስትር አብደላ ሃምዶክ ከስልጣን ከተነሱበት እ አ አ ከጥቅምት ሃያ አምስት ቀን ጀምረው በቁም እስር ላይ ቆይተዋል። የመንግሥት ግልበጣውን ተከትሎ በተቀሰቀሱት ግዙፍ የተቃውሞ ሰልፎች ላይ ቢያንስ አርባ ሰዎች በጸጥታ ኃይሎች እጅ እንደተገደሉ የሱዳን ሀኪሞች ማህበር የተባለው የተቃውሞው ደጋፊ ቡድን አመልክቷል

XS
SM
MD
LG