በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ኢነፍ ፕሮጀክት ኻርቱምን በሙስናና በሁከተኛ ሌብነት ከሰሰ


The Enough Project - logo
The Enough Project - logo

የሱዳንን መንግሥት በሙስናና የሃገሪቱን ነዳጅ፣ ወርቅና መሬት በመዝረፍ የሚከስስ ሪፖርት ወጣ፡፡

የሱዳንን መንግሥት በሙስናና የሃገሪቱን ነዳጅ፣ ወርቅና መሬት በመዝረፍ የሚከስስ ሪፖርት ወጣ፡፡

ሪፖርቱን ያወጣው ተቀማጭነቱ ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ የሆነ “ኢነፍ” ፕሮጀክት የሚባል ተቋም ነው፡፡

የመጠሪያው ቀጥተኛ ትርጉም «ይበቃል» የሆነው ኢነፍ ፕሮጀክት የሰዎችን ጅምላ ፍጅትና በዘር ወይም በጎሣ ማንነት ላይ የተመሠረተ የጭፍጨፋ አድራጎትን የሚያቀናብሩ፣ የሚያመቻቹና የሚያካሂዱ ሰዎችን ወደ ገሃድ ተጠያቂነት በማውጣትና የፈፀሙትን አድራጎት መዘዝ እንዲጎነጩ በማድረግ ለሰላምና ለፍትህ መጠናከር የሚሠራ ተቋም መሆኑን እራሱ ይናገራል፡፡

ይህ /በአው.የዘ.አቆ./ በ2006 ዓ.ም. የተቋቋመ ፕሮጀክት መብቶችን የሚረግጡ የታጠቁ ቡድኖችና በሌብነት የተዋጡ መንግሥታት ወይም የነቀዙ አገዛዞች የሚፈፅሟቸውን የበረቱ የሙስና አድራጎቶች፤ ድንበር ዘለልና ሃገር አቋራጭ ወንጀሎችና ሽብር፤ ማዕድናትን፣ የዝኆን ጥርስ፣ አልማዝ እንዲሁም ሌሎች የተፈጥሮ ኃብቶችን ዘረፋ፣ ማግበስበስና ማከማቸትን እንደሚጋፈጥና እንደሚዋጋ የሚያመለክት ቡድን ሰሞኑን ባወጣው አዲስ ሪፖርት የሱዳንን መንግሥት በንቅዘት አድራጎቶችና በሌብነት ከስሷል፡፡

the enough project
the enough project

ከቪኦኤ ጋር ቃለ-ምልልስ ያደረጉት የኢነፍ ፕሮጀክት ከፍተኛ አማካሪ ኦማር ኢስማኢል የሱዳን መንግሥት ለዓመታት የሃገሪቱን ነጠላ ኃብት ወይም አንዳንዴም ከአንድ በላይ የኃብት ምንጮችን እንደሚጠቀምና በቀደሙ ዓመታት የነዳጅ ዘይትን ብቻ ይበዘብዝ እንደነበረ አመልክተዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን ከተገነጠለች በኋላ ግን የከርሰ ምድሩ የተፈጥሮ ዘይት ወደ ደቡብ በመሄዱ አሁን ትኩረቱ ወደ ወርቅ መዞሩንና ወርቁን ባለሥልጣናቱ ‘አዲሱ ዘይት’ እያሉ እንደሚጠሩት ጠቁመዋል፡፡

የሱዳን መንግሥት ሥልጣን ላይ በቆየባቸው ሰላሣ ዓመታት «ከአንድ ሚሊየን በላይ ሰው መገደሉን»ና ይህ አድራጎት የተፈፀመው ከአማፂዎች ጋር በተካሄዱ ውጊያዎች ሳይሆን «በዘር ፍጅት» መሆኑን የሚናገሩት የኢነፍ ፕሮጀክት ከፍተኛ አማካሪ ኦማር ኢስማኢል የዳርፉርን ጉዳይ ለማሳያ አንስተው ያ አድራጎት «ዘርን በማጥፋት ወንጀል»ነት መያዙን ጠቁመዋል፡፡

የሱዳን መንግሥት «ፈፅሟቸዋል፤ ወይም እየፈፀማቸው ናቸው» ሲሉ ኦማር ኢስማኤል የጠቆሟቸው አድራጎቶች በዓለም ዙሪያ የተወገዙ መሆናቸውን አመልክተው የሱዳን መንግሥትም «በራሱ ሕዝብ ላይ ጦርነት የሚያካሂድ መንግሥት ነው» ሲሉ ከስሰዋል፡፡

የኢነፍ ፕሮጀክት ዋና አማካሪ «በሁከተኛ ሌብነት የተዋጠ» ሲሉ የጠሩት የኦማር ሃሰን አል በሺር መንግሥት ሽብር ፈጠራን ለመዋጋት ከዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ ጋር ለመተባበር እና በሃገር ውሰጥ ለውጥ ለማምጣትም ለውይይት ለመቀመጥ ዝግጁ መሆኑን ስለመግለፁ እውቅና ይሰጡት ወይም ምሥጋና ይቸሩት እንደሆነ ሲጠየቁ የሱዳን መንግሥት ያንን የሚያደርገው «ለሱዳን ወይም ለሱዳን ሕዝብ ሳይሆን የራሱን ዕድሜ ለማራዘም የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከዓለምአቀፍ ማኅበረሰብ ለማግኘት ነው» ብለዋል፡፡

ኦማር ኢስማኤል አክለውም «ይህ እራሱ ሽብርተኛ የነበረ መንግሥት አሁንም ይሁን ከቀደሙት የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ጋር እተባበራለሁ የሚለው በራሱ ሕዝብ ላይ ሽብር ለመንዛት የሚያስችለውን አቅም ለማግኘት ነው» ብለዋል፡፡

«ለሰላሣ ዓመታት በአምባገነንነት ሲገዛ የኖረ መንግሥት» በራሱ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ብሎ ፕሮጀክታቸው እንደማያምን የኢነፍ ከፍተኛ አማካሪ አመልክተው «ሁሉም ተቃዋሚዎች የሚሣተፉበት ሕገ-መንግሥታዊ ጉባዔ እንዲጠራ፤ ዓለምአቀፍ የሰላም ሂደት እንዲጀመርና ዩናይትድ ስቴትስ ለጉዳዩ የምትሰጠውን ትኩረት አጠናክራ ማየት» እንደሚፈልግ ተናግረዋል፡፡

ኢነፍ ፕሮጀክት ባወጣው ሪፖርት ላይ ላሰፈረው ክሥና ዋና አማካሪው ኦማር ኢስማኤል ለሰጡት መግለጫ የሱዳን መንግሥት የሚሰጠው ምላሽ ይኖር እንደሆነ ለመጠየቅ ወደ ሱዳን የማስታወቂያ ሚኒስትር አሕመድ ቢላልና ዋሺንግተን ዲሲ ወደሚገኘው የሱዳን ሪፐብሊክ ኤምባሲ ቪኦኤ ያደረጋቸው ተደጋጋሚ የስልክ ጥሪዎች ሳይመለሱ ቀርተዋል፡፡

ዝርዝሩን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ፡፡

ኢነፍ ፕሮጀክት ኻርቱምን በሙስናና በሁከተኛ ሌብነት ከሰሰ
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:52 0:00

የፌስቡክ አስተያየት መስጫ

XS
SM
MD
LG