በሱዳን የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ አንድ ወታደራዊ አዛዥና የተወሰኑ ወታደሮቻቸው ከድተው የሱዳን ሠራዊትን መቀላቀላቸው ተነግሯል። ጦርነቱ ከ18 ወራት ከጀመረ ወዲህ ወታደራዊ አዛዥ ሲከዳ የመጀመሪያው ነው ተብሏል።
የሱዳን ሠራዊት ደጋፊዎች በደቡብ ምሥራቅ በምትገኘው ኤል ገዚራ ክልል ዋና አዛዥ የነበሩትን የአቡዋጋላ ኬይካል ፎቶ በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ ሲሆን፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ በበኩሉ ጄኔራሉ ተደራድረው መክዳታቸውንና በተከታይ ወታደሮቻቸው ላይ ባደረሰው ጥቃትም ጉዳት ማድረሱን አስታውቋል።
በተለይም በመዲናዋ ሱዳን በፈጥኖ ደራሹ ኃይል ላይ የበላይነት እያገኘ መሆኑን በማስታወቅ ላይ ያለው የሱዳን ሠራዊት፣ አቡዋጋላ ኬይካል የከዱት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ “አውዳሚ አጀንዳ” ስላለው ነው ብሏል።
ከጦርነቱ በፊት የወታደራዊ ደህንነት ባልደረባ ከነበሩት አቡዋጋላ ኬይካል ወዲያውኑ የተሰጠ አስተያየት የለም።
ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ከሱዳን ሠራዊት ጋራ በሚያደርገው ጦርነት ሰፊ አካባቢን የተቆጣጠረ ሲሆን፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው ጦርነቱ በዓለም “አስከፊ” ሲል የገለፀው የሰብዓዊ ቀውስ አስከትሏል።
ከአስር ሚሊዮን በላይ ሰዎች ሲፈናቀሉ፣ በተወሰነው የሃሪቱ ክፍል ረሃብ ተከስቷል። የውጪ ኃይሎች ደግሞ ለሁለቱም ወገኖች ቁሳዊ ድጋፍ በማድረግ ላይ እንደሆኑ ተነግሯል።
መድረክ / ፎረም