በዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲዎች፣ “ለጋዛ አጋርነት” በሚል ፍልስጥኤማውያንን በመደገፍ የተጀመረው የተማሪዎች ተቃውሞ፣ ዛሬ ዐርብ፣ በእውቁ የፓሪስ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችም ዘንድ ዳግም ተቀስቅሷል፡፡
ተቃውሞው ዛሬ የቀጠለው፣ የፈረንሳይ ፖሊስ የተማሪዎቹን የተቃውሞ ሰልፍ ከበተነ ቀናት በኋላ ነው፡፡
በሳይንስ ፖ ዩኒቨርሲቲ የሚማሩ በዐሥርት የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ በማዕከላዊ ፓሪስ የሚገኘውን የዩኒቨርሲቲውን ሕንፃ መግቢያ፣ ከቆሻሻ ማጠራቀሚያ፣ ከዕንጨት እና ከብረት በተሠሩ እቃዎች እና ብስክሌቶች በማገር ዘግተውታል።
ተማሪዎቹ፣ በጓደኞቻቸው ላይ ፖሊስን የጠራውን የዩኒቨርሲቲውን አስተዳደር በመቃወም ወደ 40 የሚደርሱ ሰልፈኞች ሌሊቱን በአንድ ሕንፃ ውስጥ በመኾን አሳልፈዋል።
በአሜሪካ የተደረገው የተማሪዎች ተቃውሞ እንዳነሣሣቸው የተናገረችው ሉዊዝ የተባለች ተማሪ፣ “ከሁሉም በፊት አንድነታችን ከፍልስጥኤም ሕዝብ ጋራ ነው፤” በማለት አጽንዖት ሰጥታለች።
ሉዊዝ ተቃውሞው፣ በሌሎች ተማሪዎች ትምህርት ላይ ጫና እንደሚፈጥር ብትገነዘብም፣ “ለራሳችን ቅድሚያ በምንሰጣቸው ነገሮች ብቻ መጨነቅ የለብንም፤” በማለት ትመክራለች፡፡
"ይህ ከእኛም በላይ ነው” የምትለው ሉዊዝ፣ “በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ መንቀሳቀስ አለብን፡፡ እንደ አካዳሚያዊ ማኅበረሰብ አባላት በዓለም ላይ ትምህርት ቤቶችን በማፈራረስና በማውደም እየተፈጸሙ ያሉ ድርጊቶች ሲኖሩ ኃላፊነት አለብንና። አሁን በጋዛ እየተፈጸመ ያለው በትክክል ይኸው ነውና፤” ብላለች፡፡
የእስራኤል-ሐማስ ጦርነትን በመቃወም፣ ከካሊፎርኒያ እስከ ከነቲኬት ባሉ የዩኒቨርሲቲ ግቢዎች እየተስፋፉ ያሉ በርካታ ሰልፎች አካል የኾነውና ዐሥረኛ ቀኑን ያስቆጠረው የኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ተቃውሞ፣ የፓሪስ ዩኒቨርሲቲዎችን አነሣስቷል።
በዩናይትድ ስቴትስ ዩኒቨርሲቲዎች የተማሪዎች ተቃውሞ፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ተማሪዎች ከፖሊስ ጋራ በተፈጠረ ግጭት መታሰራቸው ታውቋል፡፡
መድረክ / ፎረም