በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ለኢድ የታሰበው ተኩስ ማቆም ከሽፎ በካርቱም ውጊያው ቀጥሏል


ካርቱም
ካርቱም

በሱዳን የሁለቱ ተቀናቃኝ ጄኔራሎች ወታደሮች ዛሬ ዓርብ በካርቱም ጎዳናዎች ላይ ከፍተኛ ውጊያ ሲያደርጉ ውለዋል። ዛሬ ተከብሮ የዋለውን የኢድ በዓል ምክንያት በማድረግ የተኩስ ስምምነት ተደርጎ የነበረ ቢሆንም፣ ሳይከበር ቀርቷል።

በሱዳን ጦር ጠቅላይ አዛዥ ጄነራል አብደል ፈታህ አል ቡርሃን እና በአርኤስኤፍ መሪ ጀነራል ሞሃመድ አምዳን ደጋሎ ወይም ኽመቲ ወታደሮች መካከል ካለፈው ቅዳሜ ጀምሮ፣ በተለይም በመዲናዋ ካርቱምና በሌሎችም ከተሞች በተደረገው ውጊያ፣ ከ400 በለይ ሰዎች ሲሞቱ በሺሕዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ተጎድተዋል።

የሱዳን ሓኪሞች ማኅበር እንዳለው የኢድ አል-ፈጥር በዓል በመከበር ላይ ሳለ፣ በካርቱም በርካታ ሥፍራዎች ምሽቱን በቦምብ ተደብድበዋል።

ሕዝብ በሚበዛባቸው በማዕከላዊ እና በሰሜን ካርቱም ሁለቱ ወገኖች ዛሬ ከበድ ያለ የመንገድ ላይ ውጊያ እንዳደረጉ እማኞች ለኤኤፍፒ ተናግረዋል።

የአፍሪካ ኅብረት፣ በኮሚሽኑ ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ሰብሳቢነት አስቸኳይ የሚኒስትሮች ስብሰባ በማድረግ፣ የኢድ በዓልን ምክንያት በማድረግና የሰብዓዊ ተግባር ለማከናወን እንዲሁም ወደ ዘላቂ ተኩስ አቁም ለማምራት እንዲቻል ለአንድ ሳምንት የሚቆይ የትኩስ አቁም እንዲደረግ ጠይቆ የነበረ መሆኑን ኅብረቱ ትናንት ያወጣው መግለጫ አመልክቷል።

የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዥ እና የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ሚኒስርት አንተኒ ብሊንከን፣ ሁለቱን ወገኖች ለየብቻ በስልክ አግኝተው፣ የኢድ አል-ፈጥር በዓልን ምክንያት በማድረግ ቢያንስ ለሦስት ቀናት የተኩስ ማቆም እንዲደረግ ጠይቀው የነበረ ቢሆንም፣ በካርቱም ፍንዳታውና ተኩሱ ቀጥሏል።

XS
SM
MD
LG