በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የሰዎች ህገወጥ ዝውውር እንዲገታ ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ ተማጸኑ


የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ
የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ

ሜዲተራኒያን ባህር ላይ የሚፈጸመውን ህገ ወጥ የሰው ዝውውር የአካባቢው ሀገሮች ባለሥልጣናት እንዲያስቆሙ የሮማ ካቶሊክ ቤተ ክርስቲያን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳት ፍራንሲስ አሳሰቡ፡፡

ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱ ተማጽኖውን ያቀረቡት ጣሊያን ባህር ጠረፍ ላይ የበርካታ ፍልሰተኞች ህይወት የጠፋበትን የጀልባ አደጋ ተከትሎ ነው፡፡

ትናንት ዕሁድ በቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን ባሰሙት ቃል “ከአሁን ወዲያ እንዲህ ያለው አሳዛኝ አደጋ እንዳይደርስ እንከላከል ብዬ እንደገና እማጸናለሁ” ብለዋል፡፡

ባለፈው ሳምንት ፍልሰተኞች ይዞ ሲጓዝ ጣሊያን ካላቢሪያን ጠረፍ ላይ በሰጠመው ጀልባ ላይ ከነበሩ ውስጥ እስካሁን የ70 ሰዎች አስከሬኖች መገኘታቸውን የአካባቢው ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡ ከቱርክ የተነሳው ጀልባ ላይ ሶማሊያ፡ ሶሪያ፡ አፍጋኒስታን፡ ኢራን እና ፓኪስታንን ጨምሮ የተለያዩ ሀገሮች ዜጎች አሳፍሮ እንደነበር ተመልክቷል፡፡

የአካባቢው ባለሥልጣናት እንደገመቱት ጀልባው ወደ 200 የሚጠጉ ፍልሰተኞች አሳፍሮ የነበረ ሲሆን 80 የሚሆኑት ህይወታቸውን ለማትረፍ ተችሏል፡፡

ከዚህ አደጋ በተያይዘ ሶስት ህገወጥ አዘዋዋሪዎች በዚህ ሳምንት መታሰራቸው ተመልክቷል፡፡ ለአደጋው ሠለባዎች በፍጥነት አልተደረሰላቸውም የሚሉ ውንጀላዎች መቅረባቸውን ተከትሎ ስለተሰጠው ምላሽ ምርመራ መከፈቱን የሮይተርስ ዘገባ ጨምሮ አስረድቷል፡፡

የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጂርጂያ ሜሎኒ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገሮች ህገ ወጥ ፍልሰትን ለመግታት ዕርምጃ እንዲወስዱ ጠይቀው የካቶሊካዊት ቤተ ክርስቲያኒቱን ርዕሰ ሊቃነ ጳጳሳቱንም ስላቀረቡት ተማጽኖ አመስግነዋል፡፡

XS
SM
MD
LG