በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ማይክ ሐመር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ሆኑ


የዩኤስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር
የዩኤስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር

አምባሳደር ማይክ ሐመር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ሆነው መሾማቸውን የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ዛሬ አስታወቁ።

የመሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ቢሮ ባወጣው የብሊንከን የፅሁፍ መግለጫ አምባሳደር ሐመር አሁን እያገለገሉ ያሉትን አምባሳደር ዴቪድ ስታተርፊልድን እንደሚተኩ ተገልጿል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ በመግለጫቸው “አምባሳደር ስታተርፊልድ ለተመደቡበት ኃላፊነት ስላዋሉት ልምድና ስላሳዩት ቁርጠኛነት” አመስግነው “አምባሳደር ሐመርም አፍሪካ ቀንድ ውስጥ ለምናደርገው ጥረት የሚሰጡትን ጉልበትና ራዕይም በጉጉት እጠባበቃለሁ” ብለዋል።

የሐመር መሾም ዩናይትድ ስቴትስ በአካባቢው እያደረገች ያለችውን ዲፕሎማሲያዊ ጥረት መጠናከር መንግሥታቸው ያለውን ቁርጠኝነት እንደሚያሳይ ብሊንከን በመግለጫቸው አመልክተዋል። “ከሁሉም በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ወደ ሰላም የሚወስደውን ሁሉን አካታች የሆነ የፖለቲካ ሂደት፣ የጋራ ደኅንነትና የመላ ኢትዮጵያዊያንን ብልጽግናን የሚደግፍ ነው” ብለዋል ብሊንከን።

አስተዳደራቸው “መላ ትኩረቱን ግጭት እንዲቆም፣ ሰብዓዊ ድጋፍ ባልተገደበ ሁኔታ እንዲደርስ፣ በሁሉም ወገኖች በተፈፀሙ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችና ጥቃቶች ላይ ግልፅ ምርመራ እንዲደረግና ለግጭቱ መፍትሄ ለማምጣት ድርድር እንዲካሄድ ያደርጋል” ብለዋል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ።

በሌላ በኩል የአፍሪካ ኅብረት ልዩ ልዑክ ኦሉሴጉን ኦባሳንጆ መቀሌ ላይ ከዶ/ር ደብረፅዮን ገብረሚካዔል ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውን የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ ትናንት ባወጡት ትዊት አመልክተዋል።

XS
SM
MD
LG