በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የባይደን መልዕክት ለዓለም የሰብዓዊነት ቀን


የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን
የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን

“በዓለም ዙሪያ በሰብዓዊ የበጎ አድራጎት ሥራ ላይ የተሠማሩ ሥራቸውን ሲያከናውኑ የእኛን ጥበቃና ድጋፍ የሚፈልጉ ሁሉ በዛሬው ዕለት እናከብራቸዋለን” ሲሉ የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዓርብ ባወጡት መልዕክት አስታውቀዋል።

መልዕክታቸውን ባለፈው ዓርብ፤ ነኀሴ 13 የዋለውን የዓለም የሰብዓዊነት ቀን አስመልክተው ባይደን ባወጡትና ዋይ ሃውስ በዌብሳይቱ ላይ ባሰፈረው በዚሁ መልዕክት ከ19 ዓመታት በፊት ባግዳድ ላይ በተፈፀመ የሽብር ጥቃት ህይወታቸውን ያጡትን የሰብዓዊ ረድዔት ሠራተኞች አስታውሰው “በዚህ ቀን እነርሱንና ሌሎች በሺህ የሚቆጠሩ ህይወታቸውን ያጡ፣ የተጎዱ እና የታገቱ የእርዳታ ሠራተኞችን እናስባለን” ብለዋል።

ዓለም ታይቶ የማይታወቅ የሰብዓዊ አገልግሎት ድጋፍ እየፈለገ ባለበት በዚህ ዓመት ከሦስት መቶ ሺህ በላይ ሰው ንፁህ ውኃ፣ መድኃኒት፣ መጠለያ፣ ምግብ፣ የደኅንነት ጥበቃና ሌሎችም አገልግሎቶች እንደሚያስፈልጉት፣ ከመቶ ሚሊየን በላይ ሰው መፈናቀሉን፣ በመቶዎች ሚሊየኖች የሚቆጠር ሰው እየተራበ መሆኑን ፕሬዚዳንቱ ጠቁመው የረድዔት ሠራተኞች በዓለም ዙሪያ ያለውን ፈተና ሁሉ በጀግንነት እየተጋፈጡ መሆናቸውን ተናገረዋል።

አስተዳደራቸው ባለፈው ዓመት የ13 ቢሊየን ዶላር ሰብዓዊ እገዛ ማድረጉን ያስታወሱት ፕሬዚዳንት ባይደን ይህም የአፍጋን ህዝብን መሠረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት፣ ሶማሊያ ውስጥ እያሻቀበ ላለው የህፃናት ረሃብ ለመድረስ፣ ትግራይ ውስጥ በፆታ ሁከት ምክንያት የተጎዱትን ለመደገፍ፣ ዮርዳኖስ፣ ባንግላዴሽና ኮሎምቢያ ውስጥ ስደተኞችና ተፈናቃዮችን ለመንከባከብ፣ እንዲሁም የመን ውስጥ ህይወት አድን የጤና አገልግሎት ለማቅረብ መዋሉን አስታውቀዋል።

“ዩናይትድ ስቴትስ በዓለም የሰብዓዊ ዕርዳታ በማድረግ ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዝ ቢሆንም ገንዘብ ብቻውን በቂ አይደለም” ያሉት ፕሬዚዳንቱ “በየዓመቱ በመቶ የሚቆጠሩና አብዛኞቹ የሃገር ውስጥ ተወላጅ የሆኑ የዕርዳታ ሠራተኞች ግድያና እገታ ጉዳት ሲፈፀምባቸው፣ ሥራቸው ሲስተጓጎል ማየት ተቀባይነት የለውም” ብለዋል።

“ግጭቶችንና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ ለበዛው መፈናቀልና ሰብዓዊ እርዳታ ፍለጋ ምክንያት የሆኑ ዋና ሰበቦች አሁንም ሳይገቱ መቀጠላቸው ጨርሶ ተቀባይነት የለውም” ብለዋል ፕሬዚዳንቱ።

እነዚያን የመከራ መንስዔዎች ለማርገብ ዓለም በየጥጉ እንዲረባረብና ሰብዓዊ ምላሹን እንዲያጠናክር ጥሪ ያስተላለፉት ፕሬዚዳንት ባይደን “ደኅንነታቸውን በማረጋገጥ፣ የተሻለ መተካከል ላለበት፣ ለተረጋጋና ለሰላማዊ ዓለም ጥረታችንን በእጥፍ በማሳደግ፣ እንዲሁም ለተጎሳቆሉት ሁሉ ዓለምአቀፉ ማኅበረሰብ ፈጥኖ እንዲደርስ በማድረግ ለሰብዓዊ ድጋፍ ሠራተኞች ሁሉ ክብራችንን እንግለፅላቸው” ብለዋል በመልዕክታቸው መደምደሚያ።

XS
SM
MD
LG