የድርቁን ምላሽ በበላይነት የሚመራው የብሔራዊ የአደጋ መከላከልና ዝግጁነት ኮሚሺን ፀሐፊ የሆኑት የግብርና ሚኒስትር ደኤታ ምትኩ ካሣ ለአሜሪካ ድምፅ ራዲዮ በሰጡት ቃል “ሊረዱ የሚገባቸው ሰዎች የሚለዩት በእራሣቸው በአርብቶ አደሮቹና በአርሦ አደሮቹ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
“በኢትዮጵያ በድርቅ ምክንያት የሞተ ሰው የለም” ሲሉም የአንዳንድ መገናኛ ብዙኃን ዘገባዎችን በድጋሚ አስተባብለዋል።
በኤል ኒኞ ምክንያት የበልጉና የክረምቱም ዝናብ መቅረታቸው ለምግብ እጥረት የተጋለጠውና አስቸኳይ እርዳታ የሚፈልገው ሰው ቁጥር 8 ሚሊየን ሁለት መቶ ሺህ መድረሱ ተገልጿል፡፡
በአንዳንድ አካባቢዎች በድርቅ ለተገዱ ሰዎች የሚደረገው ዕርዳታ በጊዜው ያልደረሰና በመጠንም ያነሰ ስለመሆኑ የሚነሱ አስተያየቶችን አቶ ምትኩ ውድቅ አድርገዋል፡፡
“የሚሰጠው ዕርዳታ ዓለምአቀፍ ደረጃን የጠበቀ ነው” ያሉት የኮሚሺኑ ፀሐፊ አቶ ምትኩ አቅርቦቱ ለአንድ ሰው በቀን 2100 ኪሎ ካሎሪ የሚያስገኝ እንደሆነ ገልፀዋል፡፡
በወር በአንድ ጊዜ በነፍስ ወከፍ 15 ኪሎ ግራም ስንዴ፣ 1.5 ኪ.ግ ጥራጥሬ፣ ግማሽ ሊትር ዘይትና ዕድሜአቸው ከአምስት ዓመት በታች ለሆነ ሕፃናት፣ ለሚያጠቡና ለነፍሰጡር እናቶች በነፍስ ወከፍ በተጨማሪ 4.5 ኪ.ግ አልሚ ምግብ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡
ዝርዝሩን ከተያያዘው የእስክንድር ፍሬው ዘገባ ያዳምጡ፡፡