የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ማቲው ሚለር እንዳስታወቁት ብሊንከን እየተባባሰ ለሄደው የሄይቲ ቀውስ አንዳች መፍትሄ ለማፈላለግ በተያዘ ጥረት ከካሪቢያን ማሕበረሰብ - ‘ካሪኮም’ አባላት ጋር ለሚያደርጉት አስቸኳይ ስብሰባ ጃማይካ ይገኛሉ። ‘ካሪኮም’ የያዘው ይህ ዕቅድ በሃገሪቱ የተረጋጋ የፖለቲካ ሽግግር እንዲፋጠን፣ ዓለም አቀፍ ሕብረ-ብሔራዊ የደህንነት ድጋፍ ተልዕኮ እንዲሰማራ እና ብሎም ነፃና ፍትሃዊ ምርጫ እንዲካሄድ ማድረግ የሚችል ሰፊ መሰረት ያለው፤ ራሱን የቻለ መማክርት እንዲሰየም ላለፉት በርካታ ቀናት ከሄይቲ ባለድርሻ አካላት ጋር ባካሄደው ምክክር እና ከዩናይትድ ስቴትስ ጋር በመነጋገር ያዘጋጀው መሆኑ ይፋ ተደርጓል። ይሁንና ለረጅም ጊዜ ሲጠበቅ የነበረው መፍትሄ ላይሳካ ይችላል የሚል ስጋትም አለ።
ካሪኮም ባለፈው አርብ ጃማይካ ላይ ይካሄዳል ያለውን አስቸኳይ ስብሰባ ይፋ ባደረገበት ወቅት በሰጠው መግለጫ “አንዳንድ መሻሻሎችን እያየን ቢሆንም፣ አሁንም ግን ባለድርሻ አካላቱ መድረስ ከሚተበቅባቸው ሥፍራ ላይ አይደሉም” ብሏል።
የታጠቁ ወረበሎች በቅርቡ በዋና ከተማይቱ ፖርት-ፕሪንስ በሚገኙ ቁልፍ ቁልፍ የመንግስት ኢላማዎች ላይ ጥቃት ማድረሳቸው ይታወሳል። በጥቃቱም የፖሊስ ጣቢያዎችን አቃጥለዋል፣ ዋና ዋና አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያዎችን ከመዝጋታቸውም በላይ ሁለቱን የሃገሪቱን ትላልቅ እስር ቤቶች በመውረር ከ4,000 በላይ እስረኞችን ፈተው ለቀዋል።
በርካታ ሰዎች ሲገደሉ፣ ከ15,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ፡ በወረበሎቹ የተወረሩ ቀዬዎቻቸውን ጥለው በመሸሽ፡ ማደሪያች አልባ ለመሆን ተገደዋል። ለድሃ ሄይቲያውያን ሸቀጥ ያቀርቡ የነበሩት አነስተኛ መደብሮች እና የጎዳና ገበያዎች የነበራቸው ሸቀጥ እና ምርት እየተሟጠጠ ሲሆን፣ እጅግ አስፈላጊ የሚባሉ አቅርቦቶችን የያዙ በደርዘን የሚቆጠሩ ኮንቴይነሮች ሳይራገፉ የሚገኙበት በፖርቶ-ፕሪንስ ያለው ዋናው ወደብም እንደተዘጋ ይገኛል።
ይህ በእንዲህ እንዳለም፡ የሃገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት አሪየል ሄንሪ የሂስፓኒዮላን ደሴት ከሄይቲ ጋር ወደምትጋራው የዶሚኒካን ሪፑብሊክ እንዳይገቡ ከተከለከሉ በኋላ፡ ባለፈው ሳምንት ወደ ፖርቶሪኮ ማቅናቸው ይታወሳል።
መድረክ / ፎረም