በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አፋር ውስጥ የተጀመረው ውጊያ እንደሚያሳስባት አሜሪካ ገልፀች


የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ
የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ

የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ እንዲነሳ የኢትዮጵያ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለፓርላማው ሃሳብ ማቅረቡን ዩናይትድ ስቴትስ እንደምታደንቅ አስታወቀች።

የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ አፋር ውስጥ ያለው ውጊያ ሃገራቸውን በጣም እንደሚያሳስባትም ገልፀዋል።

ህወሓት ሰሞኑን አፋር ውስጥ የመንግሥት ወገን ባላቸው ኃይሎች ላይ ማጥቃት መክፈቱን ማሳወቁንና ዕርዳታ መቀሌ እንዲገባ መደረጉን አስመልክቶ እንዲሁም ዩናይትድ ስቴትስ በያዘቻቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶችና በሌሎችም ጉዳዮች ላይ ማብራሪያ እንዲሰጡ ከጋዜጠኛ ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ የፀብ ሁኔታዎች ሁሉ በአፋጣኝ እንዲቆሙ፣ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶች ክሦች ላይ ግልፅ ምርመራዎች እንዲካሄዱ፣ ያልተገደበ የሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት እንዲኖርና ኢትዮጵያ ውስጥ ባሉ ግጭቶች ላይ በድርድር መፍትኄ ላይ እንዲደረስ መንግሥታቸው ሲጎተጉት መቆየቱን አስታውሰዋል።

ፕራይስ በማከል “ዩናይትድ ስቴትስ ይህንን የምታደርገው በአካባቢው ላይ በሰው ላይ በሚያደርሰው ጉዳት ምክንያት ብቻ ሳይሆን ለመላ የአፍሪካ ቀንድ የሰላም፣ የፀጥታና ደኅንነትም ሥጋትም ጭምር በመሆኑ ነው” ብለዋል።

አፋር ውስጥ ያገረሸውን ውጊያ በተመለከተ የሚወጡ ዘገባዎችም እጅግ አሳሳቢ መሆናቸውን ራይስ ጠቁመው እጅግ አስፈላጊ የሆነ እርዳታ አቅርቦትን ማስተጓጎልን ጭምር የሚያስከትሉትን የማጥቃት እንቅስቃሴዎች ሁሉም ወገኖች በአፋጣኝ እንዲያቆሙ ዩናይትድ ስቴትስ በድጋሚ እንደምታሳስብ ተናግረዋል።

ሃገር አቀፉን የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅ ለማቋረጥ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ጥር 18 የደረሰበትን ውሳኔ ሃገራቸው እንደምታደንቅና የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤቱም በአፋጣኝ እንደሚያፀድቀው ያላትን ተስፋም ገልፀው በአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጁ የተያዙ ሰዎች ሁሉም እንዲለቀቁ ጥሪ እንደምታደርግ አመልክተዋል።

"ለበለፀገችና ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያ የጋራ ራዕይን በሚያራምድ ሁሉን አቀፍ ብሄራዊ ውይይት ውስጥም ሁሉም ፓርቲዎች እንዲሳተፉ እናበረታታለን" ብለዋል ኔድ ራይስ። እነዚህ ውይይቶችም ለአጠቃላይና ግልፅ የፍትህ አሠራሮች ቁርጠኛነትን እንዲያካትቱም አሳስበዋል።

ባለፉት ጥቂት ቀናት የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ጉዳዮች ረዳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶሊ ፊ እና የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ዴቪድ ሳተርፊልድ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና ከሌሎችም የመንግሥቱ ባለሥልጣናት ጋር "ፍሬያማ" ያሏቸውን ውይይቶች ማድረጋቸውንና ዩናይትድ ስቴትስ ለኢትዮጵያ አንድነት፣ ሉዓላዊነትና የግዛት ጥብቅነት ያላትን ቁርጠኛ አቋምም ረዳት ሚኒስትሯና ልዩ ልዑኩ ለኢትዮጵያዊያኑ ባለሥልጣናት የገለፁላቸው መሆኑን ቃል አቀባዩ ገልፀዋል።

የአሜሪካዊያኑ ከፍተኛ ባለሥልጣናት የኢትዮጵያ ጉዞ ፕሬዚዳንት ባይደንና ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ያደረጉትን "ገንቢ" ያሉትን የስልክ ንግግር የተከተለ መሆኑንም ራይስ አስታውሰው የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “አሁን ተከፍቷል ብለን የምናምነውን የሰላም ዕድል ፀብን በማስወገድ፣ ተኩስ ለማቆም በመደራደር፣ እሥረኞችን ሁሉ በመልቀቅ፣ እርዳታ ባልተስተጓጎለ ሁኔታ መድረስ እንዲችል አቅርቦቱን እንደገና በማስጀመር፣ ሁሉንም ፓርቲዎች ያካተተ ብሄራዊ ውይይት በማካሄድ አጋጣሚውን እንዲጠቀሙ ለማበረታታት አውለውታል” ብለዋል።

"በመሠረቱ - አሉ የውጭ ጉዳዩ ቃል አቀባይ ኔድ ፕራይስ በማጠቃለያቸው - ይህ ግጭት የፈጠረውን የተስፋፋ እንግልትና የሰብዓዊ መብቶች ረገጣዎችን ለማስቆም እጅግ ተመራጩ መንገድ ይሄ ነው ብለን እናምናለን።"

"ለዚህም ነው በተጠናከረ ዲፕሎማሲ የምንገፋው፤ ለዚህም ነው ለዚህ መንገድ ተቀባይነት የምንሟገተው" ብለዋል ፕራይስ።

ዘገባውን ከተያያዘው የድምፅ ፋይል ያዳምጡ።

አፋር ውስጥ የተጀመረው ውጊያ እንደሚያሳስባት አሜሪካ ገልፀች
please wait

No media source currently available

0:00 0:04:48 0:00


XS
SM
MD
LG