በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሰንዓ በርዳታ ተቀባዮች በተፈጠረ መጨናነቅ ከ78 በላይ ሰዎች ሞቱ


በየመን ዋና ከተማ ሰንዓ ውስጥ፣ ለችግረኞች የገንዘብ ርዳታ ለማከፋፈል በታቀደ ዝግጅት ላይ በተፈጠረ መጨናንቅ፣ ቢያንስ የ78 ሰዎች ሕይወት ማለፉ ተዘገበ፡፡

የገንዘብ ዕደላውን ለመቀበል የተሰበሰቡት ሰዎች፣ በተኩስ ድምፅ እና በኤሌክትሪክ መሥመር ፍንዳታ ተሸብረው ሲሯሯጡ በተፈጠረው መጨናነቅ፣ ቢያንስ 78 ሰዎች ሲሞቱ ሌሎች 73 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን፣ እማኞች እና የሁቲ ዐማፅያን ባለሥልጣናት ገልጸዋል፡፡

የታጠቁ ሁቲዎች፣ ርዳታ ለመቀበል የተሰበሰበውን ሕዝብ ለመቆጣጠር ወደ ሰማይ ሲተኩሱ፣ የኤሌክትሪክ መሥመር በመምታታቸው፣ ፍንዳታ ማስከተሉን የዐይን እማኞቹ አስረድተዋል፡፡

ኹኔታው በፈጠረው ፍርሃት በርካታ ሰዎች ሲሯሯጡ፣ ከእነርሱም በብዛት የተገኙት ሴቶች እና ሕፃናት መረጋገጣቸውን፣ እማኞቹ ገልጸዋል፡፡ በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ላይ በተሠራጩ ቪዲዮዎች፥ መሬት ላይ የወደቁ አስከሬኖች እና የድረሱልን ጩኸት የሚያሰሙ የተጎዱ ሰዎች፣ እንዲሁም ለመርዳት የሚሞክሩ ሰዎች ይታያሉ፡፡

በሁቲ ዐማፅያን ቡድን የሚመራው የአገር አስተዳደር ሚኒስቴር እንዳለው፣ አደጋው የደረሰው፥ ነጋዴዎች በመሀል ከተማዋ ያሰናዱትን ርዳታ ለመመጽወት፣ በመቶዎች የተቆጠሩ ችግረኞች እንደተሰባሰቡ መሆኑ ተመልክቷል፡፡ ሚኒስቴሩ፣ በኢድ አል ፈጢር በዓል ዋዜማ ለደረሰው አደጋ ምክንያቱ፣ ዝግጅቱ ከከተማዋ ባለሥልጣናት ጋራ ሳይቀናጅ መካሔዱ ነው፤ ብሏል፡፡

XS
SM
MD
LG