በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በሜካ ብዙ ሕይወት ጠፋ፤ ብዙ ሰው ተጎዳ


በሳዑዲ አረቢያ ሚና ከተማ በትንሹ 717 የሚሆኑ ሰዎች በሐጅ በዓል ላይ በደረሰ ትርምስና መረጋገጥ ምክንያት ሞቱ፡፡

ሳዑዲ አረቢያ ዛሬ በተካሄደው ዓመታዊው የሐጅ በዓል ላይ በደረሰ ትርምስና መረጋገጥ፥ በትንሹ 717 ሰው ሲሞት ከ 805 በላይ ሌሎች ጉዳት ደርሶባቸዋል።

በሀገሪቱ ባለሥልጣናት መግለጫ መሠረት፥ ዛሬ በሚና ከተማ አደጋው የደረሰው ምዕመናን የሰይጣን ምልክቶች፣ ሰራይ ወይም ሟርት እያሉ የሚጠሯቸውን አምዶች በጠጠር እየወገሩ በነበሩበት ወቅት ነው።

ሁለት ሚሊዮን ሙስሊሞች ለፀሎት የተሰባሰቡበት የአራፋት ኮረብታ ሸለቆ ነብዩ መሐመድ ከ1,400 ዓመታት በፊት በሙስሊሞች መካከል እኩልነትና አንድነት እንዲኖር ለመጨረሻ ጊዜ ያስተማሩበት መሆኑ ይታመናል።

የሳዑዲ አረቢያ የሲቪል መከላከያ ዳይሬክተር የሰለባዎቹን ቁጥርና በቃሬዛ ላይ ያሉ ሰዎች እርዳታ ሲሰጣቸው የሚያሳዩ ምስሎችን በትዊተር (Twitter) አሠራጭተዋል፡፡

በሳዑዲ አረቢያ ባለፉት 25 ዓመታት የሐጅ በዓል ሲከበር በርካታ የሕዝብ መተራመስና መረጋገጥ ደርሶ ብዙ ሕይወት ጠፍቷል።

ከሁሉም የከፋው ነው የተባለው የደረሰው 1,400 ያለቁበት የ 1990ው አደጋ መሆኑ ይታወቃል።

ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው ክብረ በዓል ምዕመናን በሜካ ታላቁ መስጊድ የሚገኘውን ጥቁር ካባ እየዞሩ ፀሎት ያደርሳሉ።

አቅማቸው የሚፈቅድ ሙስሊሞች ሁሉ በሕይወት ዘመናቸው አንዴ በዚህ ከእምነቱ ምሰሶዎች አንዱ በሆነው የፀሎት ሂደት እንዲሣተፉ ይጠየቃሉ።

XS
SM
MD
LG