በሁለት የደቡብ ሱዳን ህዝብ ነጻ አውጭ ጦር ተቃዋሚ አንጃ ሁለት ወገኖች መካከል ዩኒቲ እና አፐር ናይል ክፍለ ሀገሮች ውስጥ የተደረገው ደም ያፋሰሰ ውጊያ በደካማው የሀገሪቱ ሰላም ላይ የባሰ አደጋ መደቀኑን ተኩስ አቁሙን የሚቆጣጠረው አካል አስታወቀ።
የደቡብ ሱዳን ተኩስ አቁም እና ደህንነት ስርዓት ተቆጣጣሪው አካል ሊቀ መንበር አስራት ዴኔሮ ትናንት ጁባ ላይ በተካሄደው ስብሰባ ላይ ባደረጉት ንግግር የሲሞን ጋትዊክ ታማኝ ኃይሎች እና የምክትል ፕሬዚዳንቱ የሪያክ ማቻር ታማኝ ኃይሎች በሁለቱ ስፍራዎች ካለፈው የካቲት አጋማሽ ጀምረው እየተዋጉ በመሆኑ ውጥረት እንዳለ ገልጸዋል
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የደቡብ ሱዳን ተልዕኮ ሰኞ ዕለት ባወጣው መግለጫ በዩኒቲ ክፍለ ግዛት ከየካቲት ጀምሮ እስከአሁን ሚያዝያ ወር ባለው ጊዜ ቢያንስ ሰባ ሁለት ሰላማዊ ሰዎች መገደላቸውን እና ስድሳ አራት አዋቂ ሴቶች እና ልጃገረዶች መደፈራቸውን ገልጿል።