በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የስሪላንካ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ስለአዲስ መንግሥት ምስረታ ውይይት ይዘዋል


በብዙ ሺዎች የተቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ቅዳሜ ዕለት ፕሬዚዳንቱ የሚኖሩበት ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ ኮሎምቦ ስሪላንካ እአአ ሐምሌ 2/2022
በብዙ ሺዎች የተቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ቅዳሜ ዕለት ፕሬዚዳንቱ የሚኖሩበት ቤተ መንግሥት ፊት ለፊት የተቃውሞ ድምፅ ሲያሰሙ ኮሎምቦ ስሪላንካ እአአ ሐምሌ 2/2022

በስሪላንካ ህዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ ፕሬዚዳንቱ ጎታባያ ራጃፕካሳ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራኒል ዊክሬሜሲንግ ሥልጣናቸውን ሊለቅቁ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሽግግር መንግሥት ከተመሰረተ በኋላ የካቢኔአቸው አባላት በሙሉ እንዳለ ሥልጣን እንደሚለቅቁ ዛሬ አስታውቀዋል።

ትናንት ፕሬዚዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንለቃለን ማለታቸውን ተከትሎ የሀገሪቱ የተቀዋሚ ፓርቲዎች ስብሰባ አድርገው አዲስ መንግሥት በመመስረት ጉዳይ ላይ ተወያይተዋል።

ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ፕሬዚዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ በይፋ ሥልጣናቸውን እስከሚለቅቁ ድረስ ዋና ከተማዋ ኮሎምቦ ከሚገኘው ቤተ መንግሥት እና ከጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ አንወጣም ብለዋል።

በስሪላንካ ለወራት የዘለቀው የኢኮኖሚ ቀውስ ህዝባዊ ቁጣ ቀስቅሷል። ይህንኑ ተከትሎም በብዙ ሺዎች የተቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች ቅዳሜ ዕለት ፕሬዚዳንቱ የሚኖሩበትን ቤተ መንግሥት በመውረር ውድመት ያደረሱ ሲሆን እና በጠቅላይ ሚኒስትሩ መኖሪያ ላይ ቃጠሎ አስነስተዋል።

ፕሬዚዳንቱ እና ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን ለመልቀቅ ተስማምተዋል። ፕሬዚዳንቱ የሥልጣን ሽግግሩ ያለ እክል እንዲከናወን ተነገ ወዲያ ረቡዕ እአአ ሐምሌ 13 ቀን እለቅቃለሁ ብለው ለፓርላማ አፈ ጉባዔው ነግረዋል። ተቃዋሚ ሰልፈኞቹ ግን ሁለቱም አሁኑኑ ይልቀቁ ብለው ጠይቀዋል።

ወታደሮች ፕሬዚዳንቱን ከግዙፉ ተቃዋሚ ሰልፍ በፊት ደህንነታቸው ወደሚጠበቅበት ያልተገለጸ ሥፍራ ወስደዋቸዋል።

ፕሬዚዳንቱን ብዙዎች ሀገሪቱ ለገባችበት የኢኮኖሚ አዘቅት ተጠያቂ ያደረጓቸው ሲሆን ሥልጣን እንዲለቅቁ ለወራት ተወጥረው ከርመዋል።

ፕሬዚዳንቱ ሥልጣን እንደሚለቅቁ የተገለጸው ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሥልጣን እንደሚለቅቁ እና ሁሉንም ፓርቲዎች ያሳተፈ መንግሥት እንደሚመሰረት ካስታወቁ በኋላ ነው።

በሺዎች የተቆጠሩ የተቆጡ ተቃዋሚ ሰልፈኞች በዋና ከተማዋ ኮሎምቦ ሰልፍ ከአካሄዱ በኋላ ብዙ መቶ የሰልፉ ተካፋዮች ፕሬዚደንቱ የሚኖሩበትን ቤተ መንግሥት በመውረር በየክፍሉ በመዘዋወር ሲቀመጡ እና መፈክር ሲያሰሙ አንዳንዶቹ ሲዋኙ በማህበራዊ መገናኛዎች ላይ ታይተዋል። ፕሬዚዳንቱ ጽህፈት ቤት የገቡት ተቃዋሚዎች "የምታስቆመን መስሎህ ነበር መጣንልህ" ሲሉ ተሰምተዋል።

የስሪላንካ ባለሥልጣናት ከሰልፉ አስቀድመው ወደ ሃያ ሺህ የሚጠጉ ወታደሮች ያሰማሩ እና የቤተ መንግሥቱን ጥበቃ ያጠናከሩ ቢሆንም ሰልፈኞቹን ጥሰው ከመግባት ማስቆም አልቻሉም።

አርብ ዕለት ፖሊስ የሰዓት ዕላፊ አውጆ የነበረ ሲሆን በሲቪል ማኅበረሰብ ድርጅቶች እና ተቃዋሚ ፓርቲዎች ጠንካራ ተቃውሞ ስለቀረበ አንስቶታል።

ህንድ የተቃውሞ ሰልፉን የሚቆጣጠር ኃይል ወደስሪላንካ ልካለች ተብሎ የወጡ ሪፖርቶችን አስተባብላለች።

የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንተኒ ብሊንከን ትናንት በባንኮክ በሰጡት ቃል ዩናይትድ ስቴትስ ሁኔታውን በመከታተል ላይ እንደሆነች ገልጸዋል።

XS
SM
MD
LG