በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የተፈጥሮ ዘይት ተቃውሞ ሰልፍ ኒው ዮርክ ላይ ተካሄደ


ጥያቄውን ያቀረቡት የከርሰ ምድር ዘይትን መጠቀም እንዲቆም ግፊት ለማሳደር ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ትናንት፣ ዕሁድ ለተካሄደ ሰልፍ የወጡ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ተሟጋቾች ናቸው። እሁድ መስከረም 6/2016 ዓ.ም
ጥያቄውን ያቀረቡት የከርሰ ምድር ዘይትን መጠቀም እንዲቆም ግፊት ለማሳደር ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ትናንት፣ ዕሁድ ለተካሄደ ሰልፍ የወጡ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ተሟጋቾች ናቸው። እሁድ መስከረም 6/2016 ዓ.ም

የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የከርሰ ምድር ዘይት ጥቅም ላይ ማዋልን ማስቆም ወደሚቻልበት ሁኔታ የሚወስድ እርምጃ እንዲወስዱና ለኢፍትኃዊ የተፈጥሮ አካባቢ አያያዝ መፍትኄ እንዲያበጁ ተጠየቁ።

ጥያቄውን ያቀረቡት የከርሰ ምድር ዘይትን መጠቀም እንዲቆም ግፊት ለማሳደር ዩናይትድ ስቴትስ፣ ኒው ዮርክ ከተማ ውስጥ ትናንት፣ ዕሁድ ለተካሄደ ሰልፍ የወጡ በአስር ሺሆች የሚቆጠሩ ተሟጋቾች ናቸው።

የዓለም መሪዎች የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ሰባ ስምንተኛ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ለመካፈል ኒው ዮርክ የሚገኙ ሲሆን መሪዎቹ የአየር ንብረት ለውጥ የሚያስከትለውን ተፅዕኖ መቋቋም፣ ፍትኃዊ ሽግግርን ማፋጠን በሚቻልባቸው መላዎች ላይ የሚመሩበት የአየር ንብረት ስብሰባ ከነገ በስተያ፣ ረቡዕ እንደሚጀመር ተነግሯል።

"መሪዎች ሁልግዜ ስለመፍትኄ ይወያያሉ፤ ስለዋናው ቁልፍ ጉዳይ ግን አያነሱም። የአየር ንብረት ቀውስን እየፈጠረ ያለው የከርሰምድር ዘይትን መጠቀም ነው" ስትል በሰልፉ ላይ የተገኘችው ዩጋንዳዊት የአየር ንብረት ደኅንነት ተሟጋች ቫኔሳ ናካቴ አስተያየቷን ሰጥታለች።

“ፍራይዴይስ ፎር ፊዩቸር” የሚባል ተቋም አባል የሆነች ሌላ ሰልፈኛም በአየር ንብረት ስብሰባው ላይ ባይደን ያለመገኘታቸው ነገር እንዳሳዘናት ገልፃ “በሚቀጥለው ዓመት በሚካሄደው ምርጫ የወጣቶችን ድምፅ ማግኘት ከፈለጉ የከርሰ ምድር ዘይት ቁፋሮ፣ ብዝበዛና ጥቅም ላይ ማዋልን ማስቆም እንዳለባቸው” አሳስባለች።

ዓለም በከርሰ-ምድር ዘይትና ነዳጅ ላይ ያላት ጥገኝነት እንዲያበቃ የሚጠይቀው ንቅናቄ አካል የሆኑ ተመሳሳይ ሰልፎች በብዙ ሃገሮች ውስጥ እየተካሄዱ ነው።

ለትናንቱ የኒው ዮርክ ትዕይንት ህዝብ ቢያንስ 75 ሺህ ሰው መውጣቱን አዘጋጆቹ አስታውቀዋል።

ባለፈው ሐምሌ እስከዚያ በታሪክ ተመዝግቦ የማያውቅ የአካባቢ ግለት በዓለም ዙሪያ የደረሰ ሲሆን ቀደም ሲልም በሰኔ ካናዳ ውስጥ የተነሳው ሰደድ በካይ ጢስ መላዪቱን ኒው ዮርክና ሰሜን ምሥራቅ ዩናይትድ ስቴትስን ለቀናት ሸፍኗል።

ዩናይትድ ስቴትስ ከግዙፎቹ ዘይት አውጭና ተጠቃሚ ሃገሮች መሪዋ ስትሆን በመጭዎቹ 26 ዓመታት ውስጥ በዓለም ላይ ከሚካሄደው የከርሰ ምድር ዘይት ብዝበዛ ሲሦው በአሜሪካ ፍላጎት የሚፈፀም መሆኑን የአየር ንብረት ደኅንነት ተሟጋቾች እየተነበዩ ነው።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG