የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ማይክ ሐመር፣ ከትላንት ጀምሮ ለአንድ ሳምንት ጉብኝት ወደ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ጅቡቲ መጓዛቸውን የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አስታውቋል።
መስሪያ ቤቱ ትላንት ባወጣው መግለጫ፣ ሐመር በአዲስ አበባ በሚኖራቸው ቆይታ ከአፍሪካ ኅብረት፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ከትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ጋራ እንደሚገናኙ እና የሰሜን ኢትዮጵያውን ጦርነት ለማስቆም ስለተፈረመው የፕሪቶሪያ ስምምነት አፈፃፀም እንደሚወያዩ አስታውቋል። ያልተፈቱ ችግሮችንም በፖለቲካ ውይይት መፍታት እና ዳግም ግጭት እንዳይቀሰቀስ ማድረግ ጊዜ የማይሰጠው ጉዳይ መሆኑን እንደሚያነሱም በመግለጫው ተጠቅሷል።
የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አክሎ "ልዩ መልዕክተኛው ሐመር በአማራ እና በኦሮሚያ ክልል የሚካሄዱ ግጭቶችን ለማስቆም ውይይት ማደረግ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እና የሚፈፀሙ ሰብአዊ መብት ጥሰቶችን መመርመር አስፈላጊ መሆኑንም ይወያያሉ" ብሏል።
ሐመር በናይሮቢ በሚኖራቸው ቆይታ ከኬንያ ባለሥልጣናት ጋራ እንደሚገናኙ እና በጋራ ቀጠናዊ ፈተናዎች ዙሪያ እንደሚነጋገሩ መግለጫው ጨምሮ የጠቀሰ ሲሆን፣ በጅቡቲም በቀጠናው እና በጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ከጅቡቲ ባለሥልጣናት ጋራ እንደሚመክሩ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም