በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር ወደ ጅቡቲ ካታር እና ኢትዮጵያ ያቀናሉ


የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፣ እስከ ታኅሣሥ 6 ቀን 2016 ዓ.ም.፣ ጅቡቲ፣ ካታር እና ኢትዮጵያ ለሚኖራቸው ጉብኝት ወደ ምስራቅ አፍሪካ ይጓዛሉ።

ማይክ ሐመር፣ በጂቡቲ በሚኖራቸው ቆይታ፣ የምሥራቅ አፍሪካ በይነ መንግሥታት ባለሥልጣናትን(IGAD) 41ኛ ልዩ የመሪዎች ጉባኤ የሚሳተፉ ሲኾን፣ ከጉባኤው ጎን ለጎንም፣ ከጂቡቲ እና ከሱዳን መንግሥታት ባለሥልጣናት ጋራም ይገናኛሉ፡፡

በአፍሪካ ቀንድ የአሜሪካ ልዩ ልዑክ ማይክ ሐመር፣ በጅቡቲ በሚኖራቸው ቆይታ፥ የሱዳንን ግጭት በቀጣናዊ እና ዓለም አቀፍ ጥረቶች ለማስቆም፣ በሱዳን ዴሞክራሲያዊ ሽግግር እንዲሳካ ለማበረታታት፣ ያልተገደበ ሰብአዊ አቅርቦት እንዲሳለጥና ለግጭቱ ተጎጂዎች ተጠያቂነት እና ፍትሕ እንዲረጋገጥ ግፊት እንደሚያደርጉ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ አስታውቋል፡፡

ልዩ ልዑኩ፣ በካታር በሚኖራቸው ቆይታም፣ የዶሃ ፎረም ላይ እንደሚሳተፉ ሲገለጽ፤ በሌላ በኩል ደግሞ፣ ከካታር ባለሥልጣናት ጋራ በሱዳን ስላለው ግጭት እና የአፍሪካ ቀንድ ሰላምን አስመልክቶ በሚደረጉ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ጥረቶች ላይ ይወያያሉ፤ ተብሏል፡፡

በኢትዮጵያም፣ ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋራ የመገናኘት ዕቅድ ያላቸው ልዩ ልዑኩ፤ በሱዳንና በአጠቃላይ የቀጣናው አንገብጋቢ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ ይጠበቃል፡፡ በተጨማሪም፣ የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት፣ የፕሪቶርያውን ዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት አፈጻጸምን እንዲቀጥሉ፣ የትጥቅ መፍታት፣ ማዋሐድ እና መልሶ ማቋቋም፣ እንዲሁም የሽግግር ፍትሕ እና ተጠያቂነት ሒደቶች ላይ መሻሻል እንዲያደርጉ ያሳስባሉ፤ ተብሏል፡፡

አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ በዐማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እየተካሔዱ ያሉ ግጭቶች በውይይት እንዲፈቱ፣ በግጭቱ ተሳታፊ የኾኑ ኹሉም አካላት፣ ለሲቪሎች ደኅንነት እንዲጨነቁ፣ ከጥላቻ ንግግሮች እንዲታቀቡና ሰብአዊ መብቶችን እንዲያከብሩ አሳስበዋል፡፡

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG