በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

አምባሳደር ማይክ ሐመር ወደ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ ያመራሉ


የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር
የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር

የዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ከነገ ኀሙስ፣ ግንቦት 23 እስከ 30 ቀን ድረስ፣ ወደ ጅቡቲ እና ኢትዮጵያ እንደሚጓዙ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ፣ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስታወቋል፡፡

አምባሳደሩ በጅቡቲ ቆይታቸው፣ በዩናይትድ ስቴትስ የአፍሪካ ኮማንድ (USAFRICOM) እና በምሥራቅ አፍሪካ ጥምር ጦር (CJTF-HOA)፣ በቀውሶች ምላሽ እና ተከታታይ የደኅንነት ስጋቶችን ለማስወገድ በሚደረጉ ጥረቶች ላይ ለመነጋገር በተዘጋጀው፣ የምሥራቅ አፍሪካ የደኅንነት መድረክ ላይ እንደሚሳተፉ መግለጫው አመልክቷል፡፡

ልዩ መልእክተኛው፣ ከጅቡቲ መንግሥት ባለሥልጣናት ጋራ፣ በሁለትዮሽ ትብብር እና በአፍሪካ ቀንድ ባሉ ቀጣናዊ ጉዳዮችም ዙሪያ እንደሚነጋገሩ በመግለጫው ተጠቁሟል፡፡

ከኢጋድ ዋና ጸሐፊ ዶር. ወርቅነህ ገበየሁ ጋራ እንደሚገናኙና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት(ኢጋድ)፣ የቅርብ ጊዜ ሥራዎችንና እንቅስቃሴዎችን እንደሚገመግሙ፣ የሚኒስቴሩ መግለጫ ገልጿል፡፡ ማይክ ሐመር፣ በኢትዮጵያ ጉብኝታቸው፣ ከአፍሪካ ኅብረት ባለሥልጣናት ጋራ በመገናኘት፣ እ.ኤ.አ. ኅዳር 2 ቀን 2022 በወጣው፣ ግጭትን የማቆም ስምምነት አፈጻጸም ላይ እንደሚነጋገሩ፣ በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ባወጣው በዚኹ መግለጫው፣ ልዩ መልእክተኛው አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ከዐዲስ አበባ ቆይታቸው በተጨማሪ ወደ መቐለም እንደሚያመሩ አስታውቋል፡፡

በቆይታቸውም፣ ከኢትዮጵያ ባለሥልጣናት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች ጋራ፣ የሽግግር ፍትሕንና የተጠያቂነት ጥረቶችን፣ እንዲሁም ትጥቅ

የማስፈታት ሒደትን፣ የተፈናቃይነት እና መልሶ ማቋቋም ፕሮግራሞችን አፈጻጸም እና ቅድሚያ ሊሰጣቸው በሚገባቸው ጉዳዮች ላይ እንደሚነጋገሩ አመልክቷል፡፡

XS
SM
MD
LG