የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ አምባሳደር ማይክ ሐመር፣ ከአውሮፓዊያኑ ግንቦት 10 እስከ 19 ባሉት ቀናት፣ ከልዩ ልዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ጋራ ለመነጋገር፣ ወደ ሎስ አንጀለስ ካሊፎርኒያ እንደሚያቀኑ፣ የዩናይትድ ስቴትስ የውጭ ጉዳይ መ/ቤት አስታውቋል።
አምባሳደር ሐመር፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት ስላስቆመው የፕሪቶርያው የሰላም ስምምነት ጨምሮ፣ በአገሪቱ ውስጥ ስላሉ ለውጦች፣ ከኅብረተሰብ ክፍሎቹ ጋራ እንደሚወያዩ፣ መሥሪያ ቤቱ ለብዙኀን መገናኛ በአሠራጨው ማስገንዘቢያ ላይ ገልጿል።
አምባሳደር ሐመር፣ በሎስ አንጀለስ ቆይታቸው፣ የዐማራ፣ የኦሮሞ፣ የሶማሌ እና የትግራይ ተወላጆችን ጨምሮ፣ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ዲያስጶራ ቡድኖች ወኪሎች ጋራ እንደሚገናኙም ታውቋል። ከዚኽም ባሻገር፣“የተባበሩት የአፍሪቃ ቀንድ ሴቶች” በተሰኘው፣ የበይነ ብሔር ሴት መሪዎች ጥምረት በተሰናዳው መድረክም ይገኛሉ፡፡
በ“ባብ ሆፕ ፓትሪዮቲክ” አዳራሽ ውስጥ የሚካሔደው ዝግጅቱ፣ አምባሳደሩ ከመላው ኢትዮ አሜሪካውያን ማኅበረሰብ ጋራ የሚነጋገሩበት እንደኾነ ተመልክቷል፡፡ ይህ ዝግጅት፣ የሰላም ሒደቶችን በማበረታትና ሴቶችን በማብቃት ላይ እንደሚያተኩርም ተጠቁሟል።
በዚኹ አጋጣሚ፣ አምባሳደር ሐመር፣ ከሎስ አንጀለስ ከንቲባ ካረን ባስ እና ከዩኤስ አፍሪካ ኢንስቲትዩት ጋራ በመተባበር፣ በደቡብ ካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ(USC) የሕዝብ ዲፕሎማሲ ማዕከል ተማሪዎችን ያነጋግራሉ ተብሎ ይጠበቃል።