በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

በጎ አድራጊ ድርጅቱ 372 ፍልሰተኞችን ከሜድትሬኒያን ባህር ላይ አዳነ


ፍልሰተኞቹ ከሜድትሬኒያን ባህር ላይ
ፍልሰተኞቹ ከሜድትሬኒያን ባህር ላይ

ኦፐን አርምስ (የተዘረጉ እጆች) የተሰኘው የስፔን በጎ አድራጎት ድርጅት በደካማ ጀልባዎች ወደ አውሮፓ ለመሻገር በመሞከር ላይ የነበሩ 372 የሚሆኑ ፍልሰተኞችን ከሜድትሬኒያን ባህር ላይ ማዳኑንና፣ አንድ በአስተላላፊዎች በጥይት የተገደለን ፍልሰተኛ አስከሬን ማግኘታቸውን አሶስዬትድ ፕረስ ዘግቧል።

ኦፕን አርምስ ኡኖ የተሰኘችው የበጎ አድራጎቱ መርከብ ፍልሰተኞቹን የሚቀበል ወደብ ፍለጋ ላይ መሆኗንና፣ ከፍልሰተኞቹ ውስጥ የህክምና ዕርዳታ የሚያፈጋቸውና በውሃ ጥም ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች እንደሚገኙበት የድርጅቱ ወኪል ሎራ ላኑዛ ተናግረዋል።

መርከቧ በ24 ሰዓት ውስጥ ሦስት የማዳን ሥራዎችን ማከናወኗንና ፍልሰተኞቹ ለአራት ቀናት በባህር ላይ ቆይተው እንደነበር ዘገባው አመልክቷል።

በፍልሰተኞች የተጨናነቀችው የአስተላላፊዎች ጀልባ ከአየር ላይ ባህሩን በሚያሥሱ በጎ አድራጊ አውሮፕላን አብራሪዎች የተገኘች ሲሆን፣ የድረሱልን ጥሪ ምልክት ለማሳያት እጃቸውን ሲያውለበልቡ ፍልሰተኞችን በፎቶ ለመያዝ ችለዋል።

ከዚህኛው የማዳን ሥራ በፊት፣ 59 የሚሆኑና ከሶሪያ፣ ግብጽ፣ ሱዳንና ኤርትራ የመጡ ፍልሰተኞችን ቱኒዚያ አቅራቢያ ከሚገኝ የባህር ዳርቻ ማዳኑን ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል። ከነዚህም ውስጥ አንድ በአስተላላፊዎች ጥይት የተገደለ ፍልሰተኛ አስከሬን ማግኘታቸውን ሎራ ላኑዛ ተናግረዋል።

ኦፕን አርምስ ኡኖ የተሰኘችው የበጎ አድራጎቱ መርከብ ላይ የሚገኘው የአሶስዬትድ ፕረስ የካሜራ ባለሙያ እንዳለው የማዳን ሥራው በሚከናወንበት ግዜ ተስፋ የቆረጡ ስደተኞች ወደ ውሃው ዘለው በመግባታቸው ሥራውን ውስብስብ አድርጎታል።

XS
SM
MD
LG