በአንዲት ከእንጨት በተሠራች ጀልባ ላይ ሆነው የሜዲትሬንያን ባህርን ሲያቋርጡ የነበሩ 117 ፍልሰተኞችን ባለፈው ቅዳሜ መታደጉን ኦፕን አርምስ የተሰኘ የበጎ አድራጎት ድርጅት አስታወቀ።
ፍልሰተኞቹ ሊቮርኖ ወደተባለችው የጣልያን ወደብ እንደሚወሰዱ ይጠበቃል።
ባለፈው ሳምንት በግሪክ አቅራቢያ በደረሰ የጀልባ አደጋ 78 ፍልሰተኞች መሞታቸው ይታወሳል። አደጋው ከአፍሪካ እና መካከለኛው ምሥራቅ ግጭትንና ድህነት በመሸሽ ወደ አውሮፓ ለመሻገር የሚሞክሩት ፍልሰተኞች ሕይወታቸውን የሚያጡበትን አሳዛኝ ሁኔታ ዓለም እንደገና ትኩረት እንዲሰጠው አድርጓል።
ቅዳሜ ዕለት በህይወት የተረፉት ፍልሰተኞች ከኤርትራ፣ ሱዳን እና ሊቢያ የመጡ መሆናቸውንና 25ቱ ሴቶች ሲሆኑ፣ አንድ የሶስት ዓመት ሕጻንም እንደሚገኝበት ኦፕን አርምስ የተሰኘው በጎ አድራጊ ድርጅት በመግለጫው አስታውቋል።
ፍልሰተኞቹን የማዳን ሥራው የተከናወነው ከእኩለ ሌሊት በኋላ በድቅድቅ ጨለማ መሆኑን እና ጀልባዋ ከሊቢያ ዳርቻ ተነስታ 30 ኪሜ ዘልቃ ከተጓዘች በኋላ እንደነበር ድርጅቱ ጨምሮ አስታውቋል።