በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ከ500 በላይ ፍልሰተኞች በአንድ ቀን ስፔን ገቡ


የፍሮንቴክስ ፖሊስ በጀልባዎች ተጭነው ካናሪ፣ የስፔን ደሴት የደረሱ ፍልሰተኞችን ወደ ቀይ መስቀል ማቆያ ድንኳን እየወሰዳቸው፣ እአአ ጥቅምት 2/2023
የፍሮንቴክስ ፖሊስ በጀልባዎች ተጭነው ካናሪ፣ የስፔን ደሴት የደረሱ ፍልሰተኞችን ወደ ቀይ መስቀል ማቆያ ድንኳን እየወሰዳቸው፣ እአአ ጥቅምት 2/2023

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ፣ ከዕንጨት በተሠሩ አራት ጀልባዎች ላይ የተጫኑ ከ500 በላይ ፍልሰተኞች፣ በ24 ሰዓታት ውስጥ፣ ካናሪ በተሰኘችው የስፔን ደሴት ላይ እንደደረሱ ታውቋል።

ትላንት የደረሰችው አንዷ ጀልባ ብቻ 280 ፍልሰተኞችን እንደያዘች ተነግሯል። ይህ አኀዝ፣ ፍልሰተኞች ወደ ካናሪ ደሴት መምጣት ከጀመሩበት እ.አ.አ ከ1994 ወዲህ፣ በአንድ ጀልባ የገቡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ፍልሰተኞች እንደኾኑ፣ የአገሪቱ መንግሥት ዜና ወኪል አስታውቋል።

ሌሎች በመቶ የሚቆጠሩ ፍልሰተኞች ደግሞ፣ በአገሪቱ ልዩ ልዩ ደሴቶች፣ ሰሞኑን እንደደረሱ ተመልክቷል።

በያዝነው የፈረንጆች ዓመት ያለፉት ዘጠኝ ወራት ውስጥ ብቻ፣ 15ሺሕ የሚደርሱ ፍልሰተኞች ስፔን እንደገቡ፣ የሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል። ይህም ካለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋራ ሲነጻጸር፣ የ20 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል፤ ተብሏል።

ከፍልሰተኞቹ የሚበዙት ከሴኔጋል እንደተነሡም ለመረዳት ተችሏል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ፣ ከልዩ ልዩ የአውሮፓ ሀገራት የተነሡና በመቶ የሚቆጠሩ ተማሪዎች፣ በጣሊያን ላምፔዱሳ ደሴት ከዐሥር ዓመት በፊት በደረሰ የመርከብ ላይ አደጋ ሕይወታቸው ያለፈውን 368 ፍልሰተኞች ለማሰብ፣ ትላንት ማክሰኞ በደሴቲቱ ተሰባስበዋል። ከዚያ አደጋ የተረፉትንም ፍልሰተኞች በአካል አግኝተው አነጋግረዋል።

ከኤርትራ፣ ከሶማሊያ እና ከኢትዮጵያ የመጡትን ፍልሰተኞች የያዘችው መርከብ፣ በላምፔዱሳ ደሴት አቅራቢያ ስትደርስ ተገልብጣ 368ቱ ሲሞቱ፣ 155ቱ ደግሞ ተርፈዋል። አደጋው፣ በሜዲትሬንያን ባሕር ላይ ከደረሱት አስከፊው እንደኾነ ተመዝግቧል።

መድረክ / ፎረም

XS
SM
MD
LG