ዋሺንግተን ዲሲ —
በደቡባዊ አፍሪካ በ45 ሚልዮን የሚገመቱ ሰዎች፣ የምግብ ዋስትና እንደማያገኙ፣ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ጠቁሟል። በቂና አቅማቸውን የሚመጥን ተመጣጣኝ ምግብ የማያገኙት ሰዎች ብዛት፣ ካለፈው አመት በ10 ከመቶ ከፍ ማለቱን፣ የምግብ ፕሮግራሙ አክሏል።
ለምግብ ዋስትናው እጦት ዋና ምክንያት የሆኑት፣ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ክስተት፣ ከአየር ንብራት ለውጥና የበርካታ ሃገሮች ኢኮኖሚ በመንገዳገድ ላይ የሚገኝ ከመሆኑ ጋር ተዳምሮ ነው ተብሏል።
ከሁሉም የተጎዳችው ግን ዚምባብዌ መሆንዋ ታውቋል። በሀገሪቱ የምግብ ዋስትና እጦት የገጠማቸው ሰዎች፣ እስከ ታህሳስ ወር ባለው ጊዜ ውስጥ፣ 8.6 ሚልዮን ይሆናሉ ተብሎ ይጠበቃል። የደቡባዊ አፍሪካ ቀጠና በተለይም የአየር ንብረት ለውጥ ለሚያደርሰው ጉዳት ተጋላጭ መሆኑን፣ በደቡባዊ አፍሪካ የዓለም የምግብ ፕሮግራም ሥራ አስኪያጅ ሎላ ካስትሮ ተናግረዋል።