የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዝዳንት ሳልቫኪር ደቡብ ሱዳን ነጻ ሃገር መሆኗን ካወጀችበት እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2011 አንስቶ የሃገሪቱ ብሔራዊ ደህንነት ኃላፊ ሆነው ያገለገለገሉትን ጀነራል አኮል ኩር ኩክ’ን ከሥልጣን ማንሳታቸውን መንግሥታዊው የደቡብ ሱዳን ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘገበ።
በብሔራዊ የደህንነት አገልግሎት ስር የሚገኘውን የሀገር ውስጥ ደህንነት ቢሮ ለዓመታት የመሩት ጀነራል አኮል ኩር ከሥልጣን የተነሱት የሽግግር መንግሥቱ በሀገሪቱ ሊደረግ የታቀደው ምርጫ በድጋሚ መዘግየቱን ካሳወቀ ሳምንታት በኃላ ነው። በምትካቸውም የፕሬዝዳንት ኪር ቅርብ ሰው መሆናቸው የተገለጸው አኬክ ቶንግ አልዩ፣ አዲሱ የደህንነት ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል።
ባለፈው ወር የፕሬዝዳንት ኪር ፅህፈት ቤት የሽግግር መንግሥቱ ሥልጣን ለሁለት አመት መራዘሙን እና እንደ አውሮፓውያን የዘመን አቆጣጠር 2022 መካሄድ የነበረበት ምርጫ በድጋሚ መራዘሙን በማስታወቁ ከዩናይትድ ስቴትስ እና ከሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማት ትችቶች ቀርበውበት ነበር። ሮይተርስ የመንግሥቱን ቃል አቀባይ እና የፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ቢሮ ምላሽ ለማግኘት ያደረገው ጥረት ያለማሳካቱን አስታውቋል።
ሆኖም ‘የደህንነት ኃላፊው ከሥልጣን መባረራቸው፣ በመንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን እርከኖች ውስጥ ያለውን የስልጣን ሽኩቻ ያሳያል’ ሲሉ ተንታኞች ተናግረዋል።
መድረክ / ፎረም