በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

ሀገር ተወለደ - የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ


የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ መንግሥት ዛሬ በይፋ ታውጇል፡፡

አዲሲቱ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ከግዙፍ የምጣኔ ኃብት እምቅ አቅም ጋር የዓለምን ማኅበረሰብ ዛሬ ተቀላቅላለች፡፡ ለሠላምና ለብልፅግና እጅግ የከበዱ ፈተናዎች እንደሚጠብቋት ግን እየተነገረ ነው፡፡

የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የቀድሞይቱን አሃዳዊ ሱዳን ከሠሃራ በታች ሦስተኛዋ ታላቅ ነዳጅ አምራች ሃገር ያደረጋት የተትረፈረፈ የከርሠ ምድር የድፍድፍ ዘይት ክምችት ያላት ሃገር ነች፡፡

ከስምንት እስከ 13 ሚሊየን የሚገመተው ሕዝቧ ለነፃነቱ በብርቱ አንድ ሆኖ የታየ ሲሆን ባለፈው ጥር ውሣኔ ሕዝብ 98 ከመቶ በሆነ ድምፁ መሠረት የራሱን የሱዳን ሪፐብሊክ መንግሥት አውጅዋል፡፡

ይሁን እንጂ አዲሲቱ ሃገር ባለፉ ጥቂት ወራት ውስጥ በግጭቶች ተውጣ ሰንብታለች፡፡ ውሣኔ ሕዝቡ ከተሰጠ ወዲህ እንኳ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ ቢያንስ ሰባት ታጣቂ ቡድኖች በሚንቀሣቀሱበት የደቡቡ ክልል ከ2 ሺህ 300 በላይ ደቡብ ሱዳናዊያን በተለያዩ የጎሣና የአማፂያን ግጭቶች ሣቢያ ተገድለዋል፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ የአቢዬይ ክፍለሃገርና የነዳጅ ገቢው ክፍፍል ጉዳዮች በዘላቂነት ካልተፈቱ ደቡብ ሱዳን ከኻርቱም ጋር በሌላ የአካባቢ ግጭት ውስጥ ልትዘፈቅ እንደምትችል የተደቀነ ሥጋት መኖሩም ይነገራል፡፡

አብዛኛው ሕዝቧ ፊደል ያልቆጠረ የሆነባት ደቡብ ሱዳን በዓለም እጅግ ኋላቀር ከሆኑ ሃገሮች አንዷ ስትሆን ዋና ከተማይቱ ጁባ እንኳ ያሏት የተወሰኑ ኪሎሜትሮች የተጠረጉ መንገዶች ናቸው፡፡ ይሁን እንጂ ደቡብ ሱዳናዊያን ለሃገራቸው ዕድገትና ብልፅግና ያላቸው ተስፋ በግልፅ ይንፀባረቃል፡፡

መንግሥቱ ባስተላለፈላቸው ጥሪ መሠረት ዜጎቿ ትናንት ዓርብ ምሽት ላይ በየአብያተ ክርስቲያኑና በየአደባባዩ ተሰብስበው ሻማ እያበሩ ለአዲሲቱ ሃገር ደህንነት ፀልየዋል፡፡

እንግዲህ "የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ" ተብላ የምትጠራውን የአዲሲቱን አገር መወለድ ለማብሰር እኩለ ሌሊት ላይ በሙሉ ሃገሪቱ ደወሎች አስተጋብተዋል፡፡

ይፋው የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የልደት ብሥራት በዓል የዓለምና አፍሪካዊያን የሃገር መሪዎች በተገኙበት ዛሬ ቅዳሜ በዋና ከተማይቱ ጁባ ተከናውኗል፡፡

የአዲሲቱ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የሕዝብ መዝሙር በሕብረ ዝማሬ ቡድን ተሰምቶ የሪፐብሊኳ የእንደራሴዎች ምክር ቤት መሪ የነፃነቷን አዋጅ አንብበዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ርዕሰ ብሔር ሳልቫ ኪር የሪፐብሊኳን የሽግግር ሕገመንግሥት ፈርመው በይፋ ቃለ መሃላ ፈፅመዋል፡፡

የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ለአፍሪካ 55ኛዋ፣ ለዓለም ደግሞ 193ኛዋ ነፃ ሃገር ሆናለች፡፡

ከፍተኛ ዕውቅናና ትኩረት በመሳብ ላይ የምትገኘው የደቡባዊ ሱዳኗ መዲና ጁባ ለደራ ገበያና ንግድ መዘጋጀቷንም «በጁባ ንግድ በ2011» የተሰኘው የዓለም ባንክ የቅርብ ጊዜ የጥናት ሪፖርት አመልክቷል።

በጥናቱ መሠረት ከ183 አገሮች በንግድ ሥራ አመቺነት የ159ኛውን ደረጃ የያዘችው ጁባ በህንፃ ሥራ ፍቃድና ንግድ ለመጀመር በሚያስችሉ ሁኔታዎች አንፃራዊ ከፍተኛ ደረጃ ያስመዘገበች ሲሆን የግብር ክፍያንና የሥራ ተቋራጮችን ተግባራዊነት በማስፈፀምም ከኬንያ፥ ከግብፅና ከናይጄሪያ ልቃ ተገኝታለች።

በሌላ በኩል ደግሞ አዲሲቱ ደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ በመጭው ሣምንት ውስጥ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አባል ሃገር እንደምትሆን የወቅቱ የፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት የሆኑት በድርጅቱ የጀርመን አምባሣደር ፒተር ዊቲግ አስታውቀዋል፡፡

ደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የመንግሥታቱ ድርጅት አባል እንድትሆን የፊታችን ረቡዕ ሐምሌ 6 ቀን ጥያቄውን እንደሚያቀርቡ የምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት አመልክተዋል፡፡

ጥያቄው ተቀባይነት ካገኘ ደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት 193ኛ አባል መንግሥት ትሆናለች፡፡

የሱዳንን ታሪክ ከጊዜው አካሄድና አወራረድ ጋር የሚዳስሰውን ጥንቅር ያዳምጡ፡፡

[ዘመናቱ የተጠቀሱት በተለየ እስካልተነገረ ድረስ በኢትዮጵያ አቆጣጠር ነው፡፡ እጅግ ቀደም ባሉ ዓመታት ለውጥ ወቅት በተወሰኑ ወራት ወደፊትና ወደኋላ ልዩነት ሊፈጠር ስለሚችል ይቅርታ እንጠይቃለን፡፡]

XS
SM
MD
LG