በቀላሉ የመሥሪያ ማገናኛዎች

የደቡብ ሱዳን አስተዳድር ከጎረቤቶቹ ጋር አብሮ ለመስራት እጁን ዘረጋ


ፕሬዝደንት ኪር የደቡብ ሱዳንን ህገመንግስት ሲፈርሙ
ፕሬዝደንት ኪር የደቡብ ሱዳንን ህገመንግስት ሲፈርሙ

ቅዳሜለት በመዲናዋ ጁባ በተደረገ ስነስርዓት በአስር ሽዎች የተቆጠሩ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ ዜጎች በአለም መሪዎች ታዛቢነት የአዲስ አገር ምስረታ በዓላቸውን አክብረዋል።

ከዋዜማው ጀምሮ ማምሻውን በጸሎትና በባህላዊ ጭፈራዎች ደምቆ ያመሸው የነጻነት ዋዜማ፤ ቅዳሜ ማለዳ ባንዲራ ይዘው ለነጻነት ክብረበዓሉ በወጡ ዜጎች ታጅቦ፣ በአለም መሪዎች ታዛቢነት ተበስሯል።

የደቡብ ሱዳን አስተዳድር ፕሬዝደንት የነበሩት ሳልቫ ኪር፤ የአዲሱቱ አገር ፕሬዝደንት ሆነው ቃለ ማሃላ ፈጽመዋል፤ ሃገሪቱ የምትተዳደርበትን ህገ-መንግስትንም በፊርማቸው አጽድቀዋል።

ፕሬዝደንት ኪር በትረ-ስልጣኑን ከተረከቡ በኋላ ባደረጉት ንግግር፤ ደቡብ ሱዳናዊያን ለዛሬዋ የነጻነት ቀን እውን መሆን ለከፈሉት መስዋእትነት ምስጋናቸውን አቅርበዋል። በተለይ የሱዳን ህዝቦች የነጻነት ጦር (SPLA) ን የመሰረቱትን ጆን ጋራንግ አመስግነዋል።

“ለ56 ዓመታት የጠበቅናት ቀን ናት። ህልማችን ዛሬ እውን ሆኗል” ብለዋል ኪር “ውድ ጓዶቼ የዛሬዋ ቀን ለነጻነት ለወደቁ ጀግንኖቻችን ልባዊ የሆነ ምስጋናና አክብሮት የምናቀርብበት ሊሆን ይገባል።”

ከዚህ ንግግር አስቀድሞ የሱዳኑ ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽር ባሰሙት ንግግር፤ የደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክን እውቅና የሰጠችው የመጀመሪያዋ አገር ሱዳን መሆኗን ተናግረዋል። ለአዲሲቷ አገር መልካም እድል የተመኙት አል-በሽር፤ መንግስታቸው አሁን ጎረቤት ከሆነችው ደቡብ ሱዳን መልካም ንግኙነት እንደሚሻም ይፋ አድርገዋል።

ደቡብና ሰሜን ሱዳን የፖለቲካና የኢኮኖሚ ፍርጫቸው የቆየ ነው። ሱዳን ከግብጽና ከብርታንያ ጥምር የቅኝ አገዛዝ እንደ እ.ኤ.አ በ1956 ዓም ነጻ ከወጣች ወዲህ በሱዳን ሰላም አልታየም።

የቀደሙ የትጥቅ ትግሎችን ተከትሎ የሱዳን ህዝቦች ነጻ አውጭ ጦር (SPLA) በዶ.ር ጆን ጋራንግ ከተመሰረተ ወዲህ፤ ከሁለት አስርት አመታት በላይ በደቡብና ሰሜን ሱዳን መካከል መሪር ውጊያ ተካሂዷል። በነዚህ የጦርነት ዘመን ደቡብ ሱዳናዊያን ተሰደዋል፣ ተርበዋል ተጠምተዋል።

“ይቅር እንላለን ግን አንረሳም!” ብለዋል ኪር።

ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር አክለውም ከጎረቤቶቻቸው ጋር በሰላም፣ በልማትና አብሮ በመስራት የሚያተኩር ግንኙነት ለመፍጠር መንግስታቸውና ህዝቦቻቸው እንደሚሰሩ ገልጸዋል።

“ከሱዳን ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ጋር እንዲሁም ከሁሉም ጎረቤቱቻችን ጋር በህብረት ከህዝባችን ጋር በጸባይም ሆነ በምግባርም የሰመረ ግንኙነት እንዲኖረን፣ በሰላም መልካም የጉርብትና እጆቻችንን እዘረጋለን” ብለዋል ፕሬዝደንት ሳልቫ ኪር።

በደቡብ ሱዳን ሪፐብሊክ የነጻነት በአል ላይ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ ባን ኪሙን፣ የሱዳኑ ፕሬዝደንት ኦማር አልበሽርና ሌሎችም የአለም መሪዎች ተገኝተዋል።

XS
SM
MD
LG