ሃገሪቱን በወታደራዊ አዋጅ ለማስተዳደር ሞክረው ያልተሳካላቸውና ክስም የቀረበባቸው የደቡብ ኮሪያው ፕሬዝደንት ዩን ሱክ ዩል ዛሬ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተነግሯል።
ዩል ለ10 ሰዓታት ያህል በሃገሪቱ የጸረ ሙስና መ/ቤት የምርምራ ጥያቄዎች ከተደረገላቸው በኋላ በመዲናዋ ሶል አቅራቢያ ወደሚገኝ እስር ቤት መወሰዳቸው ታውቋል።
በመንግሥት ላይ በማመጽ ክስ የቀረበባቸውን ፕሬዝደንት ከመኖሪያ ቤታቸው ለመያዝ ለሳምንታት ሙከራ ሲደረግ ነበር።
ከመያዛቸው በፊት የቪዲዮ መልዕክት ያስተላለፉት ዩል “በሃገሪቱ የሕግ የበላይነት ጠፍቷል” ሲሉ ተደምጠዋል።
ወታደራዊ አዋጅ ማወጃቸውም ትክክለኛ እርምጃ እንደነበርም ተናግረዋል።
ዩልን ለመያዝ ብዛት ያላቸው የፀጥታ ኅይሎች በፕሬዝደንታዊ መኖሪያቸው ተገኝተው የነበረ ሲሆን፣ የሃገሪቱ የጸረ ሙስና መ/ቤት እርሳቸውን ለመመርመር ሥልጣን ባይኖረውም ሁከትን ለማስወገድ ሲሉ ተባባሪ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በሃገሪቱ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የመጀመሪያው ፕሬዝደንት የሆኑት ዩን ሱክ ዩል ረጅም የእስር ቅጣት ሊጠብቃቸው እንደሚችል የአሶስዬትድ ፕሬስ ዘገባ አመልክቷል።
መድረክ / ፎረም